ጤና ጣቢያው ተገቢውን አገልግሎት እየሰጠን አይደለም - ተገልጋዮች

96
መቱ ግንቦት 21/2010 በኢሉአባቦር ዞን ዳሪሙ ወረዳ የሚገኘው የጎቤ ጤና ጣቢያ ተገቢውን አገልግሎት እየሰጠን አይደለም  ሲሉ ተገልጋዮች ቅሬታቸውን ገለፁ፡፡ በተገልጋዮች መብዛትና ባለሙያ እጥረት የተነሳ ችግሩ መፈጠሩን የወረዳው ጤና ጥበቃ ጽህፈት ቤት አስታውቋል፡፡ አንዳንድ ተገልጋዮች በሰጡት አስተያየት  በጤና ጣቢያው በቂ የህሙማን አልጋና መድኃኒት ባለመኖሩ ለችግር እየተዳረጉ ነው፡፡ ለጤና ጣቢያው  የተመደበው አምቡላንስም ተገቢውን አገልግሎት ስለማይሰጣቸው ህሙማንን በቃሬዛ ለማመላለስ እየተገደዱ እንደሆነ ገልፀዋል፡፡ ከተገልጋዮቹ መካከል አቶ ሻረው ገረመው  በሰጡት አስተያየት ህሙማንን ቶሎ ወደ ህክምና ለማድረስ የአምቡላንስ አገልግሎት ቢጠይቁም ምላሽ የሚሰጣቸው አካል ባለመኖሩ ለከፋ ችግር መጋለጣቸውን ተናግረዋል፡፡ “የግል ተሸከርካሪ ስናገኝ ከአቅም በላይ በሆነ ወጪ ህሙማንን ወደ ህክምና እናደርሳለን ካጣን ደግሞ በቃሬዛ ለማመላለስ እንገደዳለን” ብለዋል፡፡ በጤና ጣቢያው በቂ የህሙማን አልጋ ባለመኖሩ በተለይ ነፍሰ ጡር እናቶች ለችግር እንደሚጋለጡ የተናገሩት ደግሞ ሌላኛው አስተያየት ሰጪ አቶ ፈቃዱ ሰንበቶ ናቸው፡፡ “ሰሞኑን ለወሊድ አገልግሎት ወደ ጤና ጣቢያው  ያመጣነው የወንድሜ ባለቤት አልጋ ባለመኖሩ መሬት ላይ ሸራ ተነጥፎ ነው የተገላገለችው” በማለት እየደረሰባቸው ያለውን ችግር  ይናገራሉ፡፡ ለወሊድም ይሁን ለሌላ አስቸኳይ ህክምና ሲመጡ ወዲያው የሚያያቸው ባለሙያ ባለመኖሩ እና የሚታዘዝላቸውን መድሀኒትም ባለማግኘታቸው ለተጨማሪ እንግልት እየተዳረጉ መሆኑን የሚናገሩት ደግሞ አቶ ኢሳ ነገዎ የተባሉ አስተያየት ሰጪ ናቸው፡፡ የዳሪሙ ወረዳ ጤና ጥበቃ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ፋንታሁን ሶዮማ በበኩላቸው ለወሊድ አገልግሎት ተብሎ ከሁለት አመት በፊት የተጀመረው የተጨማሪ ክፍሎች ግንባታ በዲዛይን ችግር በመቋረጡ በወሊድ አገልግሎት አሰጣጥ  ላይ ችግር እንዳስከተለባቸው ተናግረዋል፡፡ በዚህም የተነሳ ጤና ጣቢያው ማስተናገድ ከሚገባው 25 ሺህ ሰው በእጥፍ የሚበልጥ ተገልጋይ ለማስተናገድ መገደዱ ለችግሩ መፈጠር ዋነኛ መንስኤ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ በመድሀኒት አቅርቦት በኩል የተፈጠረው ችግር በግዥ ባለሙያ እጥረት በመሆኑ ችግሩን በአፋጣኝ ለመቅረፍ ጥረት እንደሚደረግ ተናግረዋል፡፡ ያለው አምቡላንስ አንድ ብቻ በመሆኑ ከወረዳው ስፋት አኳያ ህብረተሰቡን በፍጥነት ለማገልገል ችግር እየፈጠረባቸው እንደሆነም ገልጸዋል፡፡ የወረዳው አስተዳደር ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ደረጀ በፈቃዱ እንዳሉት ግንባታው በመሀል የተቋረጠው የተጨማሪ ክፍሎች ግንባታ በአጭር ጊዜ ውስጥ ጀምሮ ለማጠናቀቅ ከዞኑ ኮንስትራክሽን ጽህፈት ቤት ጋር ጥረት እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም