የንጹህ መጠጥ ውሃ ችግራቸው በመፈታቱ መደሰታቸውን የአንኮበር ወረዳ ነዋሪዎች ገለጹ

113
ደብረ በርሃን  ግንቦት 21/2010 የነበረባቸው የንጹህ መጠጥ ውሃ አቅርቦት ችግር በመፈታቱ መደሰታቸውን በሰሜን ሸዋ ዞን አንኮበር ወረዳ  ነዋሪዎች ገለፁ። የወረዳው ውሃና ኢነርጅ ጽህፈት ቤት በበኩሉ ከ12 ሚሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ የተገነቡ ሁለት የውሃ ፕሮጀክቶች ግንባታ ተጠናቆ አገልግሎት መስጠት መጀመራቸውን አስታውቋል፡፡ በአንኮበር ወረዳ የደረፎ ቀበሌ ነዋሪ አቶ አራጋው ፈንታ በሰጡት አስተያየት ቀደም ሲል በአካባቢያቸው ውሃ ባለመኖሩ ንፁህ የመጠጥ ውሃ ለማግኘት በቀን ከሁለት እስከ ሦስት ሰዓት በእግር ይጓዙ ነበር፡፡ አሁን ከአጎራባች ቀበሌ ተስቦ በየቤታቸው በገባላቸው ቧንቧ የንጹህ መጠጥ ውሃ ተጠቃሚ በመሆናቸው ለዘመናት ያቀርቡት የነበረው ችግር እንደተፈታላቸው ገልፀዋል፡፡ የእዚሁ ቀበሌ ነዋሪ ወይዘሮ አሰለፈች በየነ በበኩላቸው በአካባቢያቸው በነበረው የውሃ እጦት በተለይ እንስሳት የሚጠጡትን ውሃ ፍለጋ ከረዥም ርቀት ለማምጣት ስለሚከብዳቸው እንስሳቱ በሦስት ቀን አንድ ጊዜ ብቻ ይጠጡ እንደነበር አስታውሰዋል፡፡ በአሁኑ ወቅት በየቤታቸው የቧንቧ ውሃ ተጠቃሚ ከመሆናቸው ባለፈ የከብት ማጠጫና የልብስ ማጠቢያ ገንዳ ተሰርቶ ተጠቃሚ በመሆናቸው መደሰታቸውን ተናግረዋል፡፡ የአይገብር ቀበሌ ነዋሪ አቶ ተክለመድን ሳህለ በበኩላቸው ቀበሌው የአፋር ጠረፋማ አካባቢ ተጎራባች በመሆኑ በአካባቢያቸው የውሃ አማራጭ አለመኖሩን ጠቁመዋል። ረዥም ርቀት ተጉዘው በግመል ለሰውና ለእንስሳት ውሃ ለመቅዳት ሲሉ ጊዜና ጉልበት ከማባከን ባለፈ በወረፋ ጥበቃ ከሰዎች ጋር ለግጭት ይዳረጉ እንደነበር አስታውሰዋል፡፡ በአሁኑ ወቅት በመንግስት፣ መንግስታዊ ባልሆኑ ድርጅቶችና በሕብረተሰቡ ተሳትፎ በተገነባው የውሃ ታንከር ችግራቸው ተፈቶ  እንስሳት ጭምር ያለችግር ውሃ በማግኘታቸው ደስተኛ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡ የአንኮበር ወረዳ ውሃና ኢነርጅ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ በለጠ ጌጡ በበኩላቸው በአካባቢው ይስተዋል የነበረው የመጠጥ ውሃ አቅርቦት የመልካም አስተዳደር ችግር ፈጥሮ መቆየቱን ተናግረዋል። ችግሩን ከግምት ውስጥ በማስገባትም በተሰራው ስራ በአሁኑ ወቅት በ12 ሚሊዮን 486 ሺህ ብር የተገነቡ ሁለት የውሃ ፕሮጀክቶች ግንባታቸው ተጠናቆ አገልግሎት መስጠት መጀመራቸውን አስረድተዋል። " የውሃ ተቋማቱ 15 ሺህ 700 ሰዎችን ተጠቃሚ የሚያደርጉ ሲሆን ከ20 ዓመት በላይ አገልግሎት መስጠት ይችላሉ " ብለዋል። ከአንኮበር ወረዳ በ11 እና 8 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ያሉ ምንጮችን በማጎልበት በየቤቱ የንጹህ ውሃ ተጠቃሚ ከማድረግ በላፈ 7 የከብት ማጠጫና 5 የልብስ ማጠቢያ ገንዳዎች መሰራታቸውን ጠቁመዋል፡፡ አቶ በለጠ እንዳሉት ግንባታቸው ተጠናቆ ለአገልግሎት የበቁት ሁለቱ የውሃ ታንከሮች 120 ሜትር ኪዩብ ውሃ የመያዝ አቅም አላቸው፡፡ የውሃ ፕሮጀክቶቹ ተጠናቀው አገልግሎት መጀመር የወረዳውን የገጠር ንጹህ መጠጥ ውሃ ሽፋን አምና ከነበረበት 64 በመቶ ወደ 71 በመቶ ከፍ እንዲል ማድረጉን አስታውቀዋል፡፡ "የሰሜን ሽዋ ዞን ውሃ፣ መስኖና ኢነርጅ ልማት መምሪያ ኃላፊ አቶ ኤፍሬም ምንሽር በበኩላቸው በተያዘው ዓመት የገጠር ንጹህ መጠጥ ውሃ ሽፋኑን ለማሳደግ ከመንግስትና መንግስታዊ ካልሆኑ ድርጅቶች 33 ነጥብ 7 ሚሊዮን ብር ተመድቦ እየተሰራ ነው" ብለዋል። እነደኃላፊው ገለጻ፣ በአሁኑ ወቅት 23 የውሃ ፕሮጀክቶች በግንባታ ሂደት ላይ ሲሆኑ ከእነዚህ ውስጥም 6ቱ ተጠናቀው አገልግሎት መስጠት ጀምረዋል፤ ቀሪዎቹም በተለያየ ደረጃ በግንባታ ላይ መሆናቸውን ነው የገለጹት። በዞኑ ቀደም ሲል የተገነቡ 531 አነስተኛ የገጠር ንጹህ መጠጥ ውሃ ተቋማት ይገኛሉ።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም