በህዝቦች መካከል ዘላቂ ሰላም እንዲነግስ የድርሻቸውን እንደሚወጡ ምሁራን ተናገሩ

49

መቀሌ የካቲት 17/2011 በህዝቦች መካከል ዘላቂ ሰላም እንዲነግስ የሰላም አቀንቃኝ በመሆን የድርሻቸውን እንደሚወጡ  ምሁራን ገለጹ፡፡

በመቀሌ ዩኒቨርስቲ አስተባበሪነት ለሁለት ቀናት ሲካሄድ የቆየው የትግራይና አማራ የህዝብና የልሂቃን/ ምሁራን/  የሰላም ውይይት ዛሬ ተጠናቀቀ።

በዚሁ ህዝባዊ ውይይት ከተሳተፉት መካከል የመቀሌ ዩኒቨርስቲ መምህር ዶክተር መሓሪ ይምላው በተለይ ለኢዜአ በሰጡት አስተያየት " በህዝቦች መካከል ግጭት ሊከሰት የሚችለው በሚፈጠሩ ማህበራዊ ግንኙነት ሂደት ውስጥ ነው " ብለዋል፡፡

በህዝቦች ማህበራዊ ግንኙነት መካከል ግጭት መፈጠሩ ተፈጥራዊ መሆኑን ያመለከቱት ዶክተር መሐሪ፣ ግጭቶች ሲፈጠሩ የሚፈቱት አግባብ ባለው እውቀት እና በነውጥ አልባ አፈታት ዘዴ መሆን እንደሚኖርበት አመልክተዋል።

በህዝቦች፣በአመራሮች አሊያም በልሂቃን መካከል የራስ ፍላጎትን ለማሟላት የሚፈጠሩ ግጭቶች ለመፍታት በቅድሚያ ለንግግር ዝግጁ መሆን፣መደማመጥና  በሂደትም  መግባባት ላይ መድረስ እንደሚሻል  ገለጸዋል።

ግጭቶችን ለመፍታት ደግሞ ጉዳዮችን ከራስ ፍላጎትና ስሜት ጋር ብቻ ማነጻጸር እንደማይገባና ሁኔታዎችን በቅንነት ተመልክቶ በመገንዘብ ሊሆን እንደሚገባም ጠቁመዋል።

ከደብረታቦር ዩኒቨርስቲ የመጡት ዶክተር ቶማስ አበራ በበኩላቸው፣ የሰላም ውይይቱ በአማራና ትግራይ ህዝቦች መካከል የነበረውን መልካም  ግንኙነት ወደ ነበረበት ሰላም ለመመለስ ጥሩ አጋጣሚ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

" በሁለቱም ክልሎች መካከል የተፈጠረው ችግር ህዝቦች እጃቸውን አለበት የሚል እምነት ፈጽሞ የለኝም " ያሉት ዶክተር ቶማስ፣ ችግሩን ለመፍታትና ውጥረቱን ለማርገብ  ልሂቃንና የፖሊቲካ አመራሮች እንደ አሁኑ ውይይት ተቀራርበው በመምከር ለመፍትሄው የድርሻቸውን መወጣት እንዳለባቸው አመልክተዋል፡፡

በህዝቦች መካከል ዘላቂ ሰላምን እንዲነግስ በአስተማሪነት  የሰላም አቀንቃኝ  በመሆን የበኩላቸውን አስተዋጽኦ እንደሚያደርጉ ምሁራኑ ተናግረዋል፡፡

በውይይቱ የተሳተፉት የኦርቶዶክስ ኃይማኖት ሊቀ ሊቃውንት አባ መልአኩ ታከለ  እንደተናገሩት ሰላም ከአእምሮ የሚመነጭ የመረጋጋት ምንጭ ነው፡፡

" የሰላም ዋጋ ከሁሉም ነገር የላቀ ነው" ያሉት አባ መልአኩ፣ግጭት ለሰላም ዋጋ ካለመስጠት የሚመነጭ በመሆኑ ምሁራን፣የኃይማኖት መሪዎችና ሌሎች የህብረተሰብ ክፍሎች በህዝቦች መካከል ሰላም እንዲነግስ  ሊሰሩ እንደሚገባ አመልክተዋል።

ልሂቃን/ምሁራን/ እውቀታቸውን ተጠቅመው ህዝቡን ማስተማርና ሊከተላቸው ማድረግ እንደሚገባ ጠቁመው እሳቸውም ለሰላም መሰፈን  የበኩላቸውን እንደሚወጡ ተናግረዋል፡፡

በውይይቱ ማጠቃለያ የተገኙት የመቀሌ ዩኒቨርስቲ ፕሬዚዳንት ፕሮፌሰር ክንደያ ገብረህይወት ዘላቂ ሰላምን የማረጋገጥ ስራ ከራስ እንደሚጀምር ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ፕሬዚዳንቶች የሰላም ፎረም አባላት እንደሆኑ ያመለከቱት ፕሮፌሰሩ " ስለሰላም ልንዘምርና በትጋት ልንሰራ ይገባል" ብለዋል።

ፕሮፌሰር ክንደያ እንዳሉት በትግራይና አማራ ህዝቦች መካከል በርካታ  የሚያግባቡዋቸው መልካም እሴቶችን እያሉ የሚያለያያቸውን በማጉላት ለግጭት ተጋላጭ እንዲሆኑ እያደረጉ ያሉትን አካላት ለመመለስ በተለይ ልሂቃን የሰላም አቅንቃኝ መሆን ሲችሉ ነው።

የሰላም ጉዞን ለማጠናከር ለሚጥሩ አካላትም አስፈላጊውን ድጋፍ ለመስጠት የመቀሌ ዩኒቨርስቲ ዝግጁ መሆኑንም አረጋግጠዋል።

በውይይቱ ከሁለቱም ክልሎች እና ከተለያዩ የሃገሪቱ ዩኒቨርስቲዎች የተወጣጡ ምሁራን፣የኃይማኖት መሪዎችና ሌሎችም የህብረተሰብ ክፍሎች ተሳትፈዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም