በሐረማያ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎችን የሰላም ባለቤት በማድረግ ሰላማዊ የመማር ማስተማር ሂደት ማስፈን ተችሏል

69

ሀረር የካቲት 16/2011 በሐረማያ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎችን የሰላም ባለቤት ለማድረግ የተከናወነው ሥራ ሰላማዊ የመማር ማስተማር ሂደት እንዲሰፍን ማድረጉን ዩኒቨርሲቲው አስታወቀ።

አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ ተማሪዎች በበኩላቸው በተቋሙ አለመግባባቶችን እርስ በርስና ከአካባቢው ማህበረሰብ ጋር በመነጋገር ለመፍታት በመቻሉ በተቋሙ ሰላማዊ የመማር ማስተማር ሂደት መስፈኑን ተናግረዋል።

የሐረማያ ዩኒቨርሲቲየአስተዳደርና ተማሪዎች ጉዳይ ምክትል ፕሬዚዳንት ፕሮፌሰር ጄይላን ወልዪ እንደገለጹት በተቋሙ ተማሪዎችና ሠራተኞች ለሰላም ባለቤት ሆነው መንቀሳቀሳቸው በመጀመርያው መንፈቅ ዓመት የመማር ማስተማር ሥራው ሰላማዊ እንዲሆን አስችሏል።

ለሃይማኖት አባቶችና ለአገር ሽማግሌዎች፣ ለአባ ገዳዎችና ወጣቶች፣ ለአካባቢው ማህበረሰብና ሌሎች አካላት በግጭት አፈታትና አወጋገድ ላይ ዩኒቨርሲቲው የሰጠው የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራም የራሱ አስተዋጽኦ እንዳለው አመልክተዋል።

ፕሮፌሰር ጄይላን እንዳሉት የዩኒቨርሲቲው ተማሪዎች በተለይ ከመመገቢያ፣ ከማደሪያ፣ ከንባብ ቤትና መሰል ተያያዥ አገልግሎቶች ጋር ባነሷቸው ጥያቄዎች ላይ በመወያየት ፈጣን ምላሽ መሰጠቱም ችግሮቹ እንዲቃለሉ አድርጓል።

ከዚህ በተጨማሪ በተቋሙ በግል የሚነሱ አለመግባባቶች ወደቡድን ጸብና ብሔር ተኮር ግጭት እንዳይቀየሩ ለተማሪው የተሰጠው ስልጠና የራሱን አስተዋጽኦ ማበርከቱን ነው የገለጹት።

እንዲሁም ተማሪን በአንድ ጊዜ ጥፋት ከመቅጣት ይልቅ ለማስተማርና ለማስማማት የተደረገው ጥረት ለውጤቱ ማማር ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማበርከቱን ተናግረዋል።

በተለይ በተቋሙ የትምህርት መጀመሪያ ወቅት ተከስቶ የነበረውን አለመግባባት  ለማስወገድ የአካባቢው ማህበረሰብ በተለይ ደግሞ አባ ገዳዎች፣ የአገር ሽማግሌዎችና የሃይማኖት አባቶች ያበረከቱት አስተዋጽዎ ከፍተኛ እንደነበር ተናግረዋል ።

በዩኒቨርሲቲው የተማሪዎች ህብረት ፕሬዚዳንት ተማሪ አማኑኤል ኢትቻ በተቋሙ በተማሪዎች መካከል ልዩነትን መሰረት ያደረጉ ግጭቶች ለመቀስቀስ በተደጋጋሚ ጊዜ ጥረት ሲደረግ እንደነበር አስታውሰዋል።

"ተማሪዎች ከተቋሙ አስተዳደር ከአባ ገዳዎች፣ ከአገር ሽማግሌዎች፣ ከሃይማኖት አባቶችና ከአካባቢው ማህበረሰብ ጋር በመሆን አለመግባባቶችን በሰላማዊ መንገድና ከወገንተኝነት በጸዳ መልኩ በመፈታቱ በመቻሉ የመጀመሪያውን የትምህርት ዘመን በሰላም እንዲጠናቀቅ አድርጓል" ብሏል።

በተለይ በተማሪዎች የተለያዩ ክበባት አማካኝነት ሰላማዊ የመማር ማስተማር ያለውን ጠቀሜታ ለተማሪዎች የሚተላለፉት መልዕክቶች ከፍተኛ አስተዋጽዎ ማበርከታቸውን ጠቁሞ ይህ ሥራ በቀጣይም ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጿል።

ከዚህ ቀደም በዩኒቨርሲቲው አልፎ አልፎ ግጭቶች ይከሰቱ ነበር፤ በአሁኑ ወቅት ግን ከአካባቢው  የሃይማናት አባቶችና አባገዳዎች እንዲሁም ከተቋሙ ሠራተኞች ጋር ተቀራርበን በመስራታችን  ሰላም ማስፈን ተችሏል" ያለው ደግሞ በተቋሙ የ3ኛ ዓመት የታሪክና ቅርስ አስተዳደር ተማሪ አሰበኝ አዳነ ነው።

የአካባቢው የአገር ሽማግሌ የሆኑት አቶ አቂል አብራሂም በበኩላቸው ሀገራዊ ለውጡን የማይፈልጉ አካላት የመማር ሥራው እንዲስተጓጎልና በተለያየ ጊዜ ሙከራ ሲያደርጉ እንደነበር አስታውሰዋል።

"የአካባቢው የአገር ሽማግሌዎችና ማህበረሰቡ ችግር ከመፈጠሩ በፊትና ከተከሰተ በኋላ በአፋጣኝ ተማሪዎችን በማነጋገር አለመግባባቶች በውይይት እንዲፈቱ በመደረጉ በተቋሙ ሰላም ሊሰፍን ተችሏል" ብለዋል።  

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም