የዩኒቨርስቲ -ኢንዱስትሪ ትስስርን ማጠናከር እንደሚገባ ተመለከተ

870

መቱ የካቲት 16/2011 የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት በተግባር የዳበረ ብቁ የሰው ኃይል እንዲያወጡ ከኢንዱስትሪው ጋር ትስስራቸውን ማጠናከር እንደሚገባ ተመለከተ፡፡

በዩኒቨርስቲ-ኢንደስትሪ ትስስር ላይ ያተኮረ የምክክር መድረክ በመቱ ዩኒቨርስቲ ተካሂዷል፡፡

የመድረኩ ተሳታፊዎች እንዳሉት ከፍተኛ የትምህርት ተቋማትና ኢንደስትሪዎች ወደ ስራ ቦታ ተልከው  በተግባር ስልጠናና ልምምድ የሚያደርጉ ተማሪዎችን ለመከታተልና ለመቆጣጠር ያላቸው ቅንጅት የላላ ነው፡፡

ከአምቦ ማዕድን ውሀ  ፋብሪካ የመጡት አቶ ደሳለኝ መኮንን በሰጡት አስተያየት ተማሪዎች ከዩኒቨርስቲ ማግኘት ስላለባቸው እውቀት በቂ ጥናትና ዝግጅት  ሳያደርጉ  የሚልኩበት አጋጣሚ ችግር መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በኢንደስትሪው  በኩል የሚታዩ የክትትልና ቁጥጥር ክፍተቶችን  በመፍታት  ረገድ የተጠናከረ ቅንጅትና መደጋገፍ ሊኖር እንደሚገባም አመልክተዋል፡፡

በዩኒቨርስቲዎችና በኢንዱስትሪ ያለው ትብብር  በተጠናከረ መመርያ ታግዞ ወደ አስገዳጅነት ቢለወጥ የበለጠ ውጤት ሊያመጣ እንደሚችል ገልጸዋል፡፡

የመቱ ዩኒቨርስቲ የምርምር ማህበረሰብ አገልግሎትና ትስስር ምክትል ፕሬዝደንት አቶ ጸጋዬ በርኬሳ እንዳሉት ተማሪዎች ለተግባር ልምምድ ወደ ኢንዱስትሪዎች  ሲላኩ  በሁለቱም ወገን የክትትልና ቁጥጥር ስራዎች አነስተኛ ነው፡፡

በከፍተኛ ትምህርት ተቋማትና ኢንደስትሪዎች መካከል ያለው ግንኙነት በጥናትና ምርምር እንዲሁም በሙያ እገዛ ሊጠናከር እንደሚገባ አመልክተዋል፡፡

” እንደ ዩኒቨርስቲ  ወደ ኢንዱስትሪዎች ሄደን የማማከር አገልግሎትና የጋራ የምርምር  በማካሄድ አሰራራቸውን እንዲያሻሽሉ እንሰራለን” ብለዋል፡፡

በሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር የዩኒቨርስቲ ኢንደስትሪ ትስስር ባለሙያ አቶ እንግዳዬ መርሻ በበኩላቸው ወደ ኢንደስትሪዎች ለተግባር ልምምድ የሚላኩ ተማሪዎች በቁጥጥር እና ቅንጅት ማነስ ተገቢውን ዕውቀት ይዞ እየወጡ አለመሆኑን ተናግረዋል፡፡

በድህረ ምረቃ ደረጃ የኢንደስትሪን ችግር የሚፈቱ የምርምር ስራዎች ውስንነት እንዳለባቸው እንደ ክፍተት የተነሳው ለማስተካከል በምክክር መድረኩ  የጋራ መግባባት ላይ ተደርሷል፡፡

ችግሮቹን ለመፍታትም  ትስስሩ የሚመራበትን መመሪያ ለማጠናከር እና ለማሻሻል በቅርቡ በሀገር አቀፍ ደረጃ ከሚመለከታቸው ባለ ድርሻ አካላት ጋር የምክክር መድረክ እንደሚዘጋጅ አመልክተዋል፡፡

” የኢንዱስትሪ ዩኒቨርስቲ ትስስር ዋነኛው መምህራንና ተማሪዎች በአገልግሎት መስጫ ተቋማት የተግባር ስልጠና የሚያገኙበትን ፣ የምርምር እና ቴክኖሎጂ ሽግግር  አሰራር ለማዘመን በትኩረት እየተሰራ ነው”  ብለዋል አቶ እንግዳዬ ፡፡

በመቱ ዩኒቨርስቲ አዘጋጅነት የተካሄደው የምክክር መድረክም በዩኒቨርስቲ -ኢንዱስትሪ ትስስር የሚስተዋሉ ችግሮችን በመለየት ወደ ፊት በጋራ ለመፍታት መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡

ለሁለት ቀናት በተዘጋጀውና ዛሬ በተጠናቀቀው የምክክር መድረክ  በሀገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች ከሚገኙ የኢንዱስትሪ ተቋማት  የተወጣጡ ተወካዮችና ባለሙያዎች የተሳተፉ ሲሆን የመቱ ዩኒቨርስቲን ልዩ ልዩ  ቤተ ሙከራዎችንም ጎብኝተዋል፡፡