በለገ ጣፎ ለገ ዳዲ ህገወጥ ቤቶችን በማፍረስ ሂደት ያጋጠሙ ችግሮችን የሚያጣራ ግብረ ኃይል ተቋቋመ

193

አዲስ አበባ  የካቲት 16/62011የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት ከሰሞኑ በለገ ጣፎ ለገ ዳዲ ከተማ በተወሰደው ህገወጥ ቤቶችን የማፍረስ ሂደት ያጋጠሙ ችግሮችን የሚያጣራ ግብረ ኃይል አቋቁሞ ወደ ስራ መግባቱን አስታወቀ።

በግብረ ኃይሉ ማጣራት ህገወጥነትን ለመከላከል በተወሰደው እርምጃ የአፈጻጸም ስህተት ከተገኘ የእርምት እርምጃ እንደሚወሰድም ገልጿል።

የክልሉ የመንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ በጉዳዩ ላይ ዛሬ መግለጫ ሰጥቷል።

የቢሮው ኃላፊ አቶ አድማሱ ዳምጠው እንዳሉት የክልሉ መንግስት የህዝቡን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ከሚከውናቸው ተግባራት መካከል የመሬት አስተዳደርና አጠቃቀም ጉዳዮች ዋነኞቹ ናቸው።

የከተማ መሬት መረጃ አያያዝ፣ ህገ ወጥ ግንባታና የመሬት ወረራን መከላከልና የኀብረተሰቡን የቤት ባለቤትነትና ተጠቃሚነት ማረጋገጥ በዘርፉ የሚሰሩ ስራዎች ናቸው።

ከዚህ በተቃራኒ የሚካሄዱ ህገወጥ ተግባራትን የመከላከሉ ስራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ነው አቶ አድማሱ የተናገሩት።

የኅብረተሰቡን ጥያቄዎች ለይቶ ወደ ጥልቅ ተሃድሶ የገባው መንግስት የህዝቡን ፍትሃዊ ተጠቃሚነት የሚጎዱ ተግባራትን መከላከል ላይ በስፋት እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

ህዝቡ ሲያነሳቸው ከነበሩ ጥያቄዎች መካከል ህገወጥ ግንባታና የመሬት ወረራን የጠቀሱት ኃላፊው የክልሉ መንግስት 25 ከተሞች ላይ ዳሰሳ በማድረግ ከ36 ሺህ በላይ በላይ ህገወጥ ቤቶችን መለየቱን ጠቁመዋል።

የዚሁ አካል የሆነው ህገወጥ ቤቶችን የማፍረስ ተግባር ሰሞኑን በለገ ጣፎ ለገ ዳዲ ከተማ መካሄዱን ተናግረዋል።

በከተማው ከ12 ሺህ በላይ ህገወጥ ቤቶች መኖራቸውን ያወሱት አቶ አድማሱ ከዚህ ውስጥ 1 ሺህ 307 ቤቶች ከከተማው ፕላን ጋር የሚቃረኑ በመሆናቸው ባለፈው ዓመት መፍረሳቸውን፣ ከከተማው ፕላን ጋር የሚስማሙ ከ5 ሺህ በላይ ቤቶች ደግሞ ወደ ህጋዊነት መዞራቸውን ጠቅሰዋል።

የሰሞኑ የማፍረስ ተግባር የተከናወነባቸው 347 ቤቶችና ያለአግባብ ታጥረው የተቀመጡ ቦታዎች መሆናቸውንና፤ ይህም ህግና ስርዓትን ተከትሎ የተወሰዱ መሆኑን ገልጸዋል።

በማፍረሱ ሂደት ችግሮች ከተፈጠሩ ያንን የሚያጣራ ግብረ ኃይል በክልሉ ፕሬዚዳንት መቋቋሙን ገልጸው የግብረ ኃይሉን ሪፖርት መሰረት በማድረግ የእርምት እርምጃዎች እንደሚወሰዱ ነው ያስታወቁት።

የክልሉ መንግስት የህግ የበላይነት የማረጋገጥን ጉዳይ ለድርድር እንደማያቀርብ የገለጹት አቶ አድማሱ ህገወጥነት ሲስፋፋ ግንባር ቀደሙ ተጎጂ ህዝቡ በመሆኑ በዚህ ጉዳይ ህዝቡም ማገዝ እንዳለበት ተናግረዋል።

በከተማው የተከናወነው የማፍረስ ተግባር ህግን መከተል አለመከተሉን ለማረጋገጥ ሰሞኑን የፌዴራልና የክልሉ ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች በስፍራው ተገኝተው እንደጎበኙት የገለጹት አቶ አድማሱ በተለይም የመገናኛ ብዙሃን በቦታው ተገኝተው እውነታውን እንዲዘግቡም ጥሪ አቅርበዋል። 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም