አድዋን ስናከብር አሁን ካለንበት የብሄርተኝነትና የመከፋፈል ስሜት ለመውጣት ቃል እየገባን መሆን አለበት-ተፎካካሪ ፓርቲዎች

65

አዲስ አበባ የካቲት 16/2011 አድዋን ስናከብር አሁን ካለንበት የብሄርተኝነትና የመከፋፈል ስሜት ለመውጣት ቃል እየገባን መሆን አለበት ሲሉ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጥሪ አቀረቡ።

"በዓሉ ኢትዮጵያዊያን የሚገጥሙንን ውስጣዊና ውጫዊ ችግሮችን በጋራ ለመፍታት የምንችልበትን አንድነት እንድናረጋግጥ ያስቻለን እንዲሁም በአህጉርና በዓለም ደረጃ ተፅዕኖ ማሳደር እንደምንችል ያሳየንበት  ነው" ሲሉም የፓርቲዎቹ አመራሮች ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ተናግረዋል።

በዘመኑ የሀገር ስጋት የነበረው የውጭ ወራሪን ለመከላከል "ትልቅ መሰዋዕት የከፈልንበት ቢሆንም ሁሉም ዜጋ በሀገሩ ጉዳይ ላይ እኩል እንደሚሰማውና እንደሚያመው እኩልም ሂይወቱን እንደሚሰጥ በተግባር አይተንበታል" ያሉት የኢትዮጵያዊያን ሀገር አቀፍ ንቅናቄ  ሊቀ መንበር ኢንጂነር ይልቃል ጌትነት ናቸው።

ሉአላዊነታችንን ከማስከበር ባለፈ ለጥቁሮች የነፃነት ምሳሌ በመሆን አህጉራዊና ዓለም አቀፋዊ ንቅንቄን መፍጠር እንደቻልን ሁሉ "በአንድነታችን ላይ በመስራት ፊታችንን ወደ ዴሞክራሲና ልማት ልንመልስ ይገባልም" ብለዋል።

ለዚህም አሁን የገጠሙንን የብሄርና የማንነት ፖለቲካ ውጥረቶች፣ የኢኮኖሚ አለመረጋጋት፣ ዓለም አቀፋዊ የኢኮኖሚና ፖለቲካ ጫና እንደ ችግር ሳንመለከት በቀና ልብ አብረን ለመፍታት አንድ የምንሆንበት አጋጣሚ አድርገን መውሰድ ይጠበቅብናል ሲሉም መልዕታቸውን አስተላልፈዋል።

የኦሮሞ ነፃነት አንድነት ግንባር ምክትል ሊቀመንበር አቶ ኡመር መሃመድ በበኩላቸው አድዋ ላይ ሁሉም ዜጋ በእኩል ዋጋ ከፍሎ ድል ማምጣቱ ሁላችንም "በአገር ጉዳይ ላይ አንድ ልብ እንዳለን የሚያሳይ የሁላችንም በዓል ነው" ብለዋል።

"በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያ የተለያዩ ችግሮች የገጠሟት ብትመስልም በሀገር ጉዳይ ላይ ግን ሁሉም ዜጋ ልዩነት እንደማይኖረው ሙሉ እምነት አለኝ" ያሉት አቶ ሙሃመድ፤  ካለፉ መልካም ታሪኮቻችን እየተማማርን ለመጪው ትውልድ ያደገች አገር ማስረከብ የግድ እንደሚልም ተናግረዋል።

"አሁን የሚታየው ዘረኝነትና ብሄርተኝነት ፋሽን በዓለም አቀፉም ፖለቲካ የሚታይ ነው" ያሉት የኢትዮጵያ ራዕይ ፓርቲ ፕሬዝዳንት አቶ ተሻለ ሰብሮ በበኩላቸው፤ አባቶቻችን አድዋ ላይ ባሳዩት የኢትዮጵያዊነት መንፈስ የአሁኑን ችግርንም ልናሸንፈው ይገባል ብለዋል።


በመሆኑም የህግ የበላይነትን በማክበርና በማስከበር፣ ብሄራዊ መግባባትን በመፍጠርና ሁላችንም እርስ በርስ በመግባባት ሁሉም ሰው የቤት ስራውን እንዲወጣ አሳስበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም