16ኛው የመላው ኢትዮጵያ ባህል ስፖርቶች ውድድር በአምቦ ከተማ ተጀመረ

59

አምቦ የካቲት16/2011 16ኛው የመላው ኢትዮጵያ ባህል ስፖርቶች ውድድርና 12ኛው የባህል ፌስቲቫል ዛሬ በአምቦ ከተማ ተጀመረ፡፡

አማራ፣ ኦሮሚያ፣ ደቡብና ሐረሪ ክልሎች እንዲሁም አዲስ አበባና ድሬዳዋ ከተማ አስተዳደርን በመወከል በውድድሩ የሚሳተፉ ከ500 በላይ ስፖርተኞች ቀርበዋል፡፡

ውድድሩ “የባህል ስፖርት ተሳትፏችን ለሰላምና ለአንድነታችን” በሚል መሪ ቃል እስከ የካቲት 24 ቀን 2011 ዓ.ም ድረስ በ12 የባህል ስፖርት አይነቶች ይካሄዳል።

በመክፈቻ ስነ ስርአቱ  ላይ በሴቶች ከ53 እስከ 57 ኪሎ ግራም ክብደት በአማራና ኦሮሚያ ክልሎች መካከል በተካሄደ የትግል ጨዋታ ውድድር  ኦሮሚያ 3 ለ 0 ዜሮ በሆነ ውጤት አሸንፏል።

የኢፌዲሪ የባህልና ቱሪዝም ሚኒስትር ዶክተር ሒሩት ካሳ በበኩላቸው ውድደሩን ሲያስጀምሩ "አባቶቻችን ጠብቀው ያስረከቡንን የባህል ስፖርት ክብር ልንሰጠውና ልንንከባከበው ይገባል" ብለዋል ።

የዘርፉ ስፖርት አይነቶች ፍቅርንና ወንድማማችነትን የሚጠነክሩና የባህል እምርታን የሚያጎለብቱ በመሆናቸው ሊበረታቱ ይገባል" ሲሉም መልእክት አሰተላልፈዋል።

የአምቦ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ ተረፈ በዳዳ በበኩላቸው የከተማና አካባቢው ነዋሪዎች ስፖርታዊ ጨዋነትን በተላበሰ መንፈስ ውድድሩን በመከታተል እንዲደግፉና እንዲያበረታቱ ጠይቀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም