በመቀሌ ከ13 ቢሊዮን ብር በላይ ካፒታል ያስመዘገቡ ባለሀብቶች የመስሪያ ቦታ ተረከቡ

81

መቀሌ የካቲት 16/2011 በመቀሌ ከተማና አካባቢው በተለያዩ የልማት ዘርፎች  ለመሰማራት ከ13 ቢሊዮን ብር በላይ ካፒታል ያስመዘገቡ ባለሀብቶችን ዛሬ የመስሪያ ቦታ ተረከቡ፡፡

በርክክብ ስነ ስርዓት ወቅት የትግራይ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ዶክተር ደብረፅዮን ገብረሚካኤል እንደገለጹት  ባለሃብቶቹ የራሳቸውን ታሪክ ለመስራት ከመቼውም ጊዜ በላይ የሚዘጋጁበት ወቅት ነው፡፡

የክልሉ መንግስት የመስሪያ ቦታውን  ከማዘጋጀት ጀምሮ በአገልግሎት አሰጣጡ የነበሩ ክፍተቶችን የማስተካከልና አዲስ አደረጃጀት መካሄዱን ተናግረዋል።

ባለሀብቶቹ በአሁኑ ወቅት በክልሉ ልማት ለመሳተፍ መወሰናቸው የአከባቢውን  ልማት በተሻለ መንገድ ለማቀላጠፍ  እንደሚያስችል ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ አስረድተዋል፡፡

" መንግስት  የኢንቨስትመንት ጥያቄዎችን  አፋጣኝ መልስ ከመስጠት በተጨማሪ መንግስት ቢሮ  ድረስ በመምጣት ያንኳኩ ባለሀብቶች ማስተናገድ ብቻ ሳይሆን ቤታቸው ድረስ በመሄድ እንጠይቃቸዋለን" ብለዋል፡፡

የከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ ኢንጂነር አርአያ ግርማይ በበኩላቸው "በከተማው በተለያዩ የስራ ዘርፎች ለመሰማራት ጥያቄ ካቀረቡ ከ800 በላይ ባለሃብቶች በመጀመሪያው ዙር እጣ የወጣላቸው 221 ባለሀብቶች ቦታቸውን ተረክበዋል "ብለዋል፡፡

ባለሀብቶቹ ወደ ግንባታ ሲገቡ ከ22ሺህ በላይ ለሚሆኑ ዜጎች የስራ እድል የፈጥራሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ አመልክተው በመጀመሪያ ዙር እጣ የወጣላቸው ባለሀብቶች 113 ሄክታር መሬት እንደተረከቡ አስረድተዋል፡፡

ኢንጂነር አርአያ እንዳሉት ባለሀብቶቹ ከ13 ቢሊዮን ብር በላይ ካፒታል ያስመዘገቡ ናቸው፡፡

" ብዙ የስራ እድል የሚፈጥር፣ወደ ውጪ ለሚላኩ ምርቶችና ለሴቶች ስራ እድል ቅድሚያ ይሰጣል፤ የፋይናንስ አቅምና የማስፈፀም አቅም በመገንባት  ሃብት ይዘው ለሚመጡ ባለሃብቶች በመሉ ይስተናገዳሉ" ብለዋል።

ካኪ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር በመኪና መገጣጠሚያና ብረታብረት ኢንዱስትሪ ለመሰማራት በ220 ሚሊዮን ብር ካፒታል በማስመዝገብ በመጀመሪያ ዙር መሬት ከተሰጣቸው ባለሀብቶች አንዱ ነው፡፡

የማህበሩ  ምክትል ስራ አስኪያጅ አቶ ገብረሚካኤል ግርማይ  በመቀሌ መዋዕለ ንዋያቸውን ለማፍሰስ ለአስተዳደሩ ባቀረቡት የቦታ ጥያቄ መሰረት እድሉ ማግኘታቸውን ተናግረዋል።

በሹራብ ማምረቻ ፋብሪካ ለመሰማራት ፈልገው ለዚህ የሚሆኑ  እቃዎች ከውጭ ከማስገባታቸው አስቀድሞ  የመስሪያ ቦታ በማግኘታቸው  መደሰታቸውን የገለጹት ደግሞ ሌላው ባለሀብት ወይዘሮ ፀሐይ ተክሉ ናቸው፡፡

ከ30 ሚሊዮን ብር በላይ  በላይ በሆነ ገንዘብ የሚቋቋመው የሽራብ ፋብሪካ 200 ለሚሆኑ ዜጎች  የስራ እድል የሚፈጥር መሆኑን ተናግረዋል።

ወጣቱ ባለሀብት ያሬድ አስገዶም  ከልማት ባንክ በተረከባቸው 200 የማሽን ሊዝ ኪራይ ታግዞ  ስራውን ለማስፋት ጠይቆ  የፈለገውን ቦታ ማግኘቱን ገልጿል፡፡

ስራውን የጀመረው ከአምስት ዓመታት በፊት 457ሺህ ብር በሆነ ካፒታል በሶስት ማሽን በመታገዝ የጨርቃ ጨርቅ ስራ በግለሰቦች መኖሪያ ቤት ተከራይቶ እንደነበር አስታውሷል፡፡

ያገኘው የመስሪያ ቦታ  የነበረበትን የቦታ ችግር እንደሚያቃልለት ገልጾ አሁን ወደ 13 ሚሊዮን ብር ያሳደገው ካፒታል ከ250 በላይ ለሚሆኑ ወገኖች የስራ እድል እንደሚፈጥር ተናግሯል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም