በካሳ ግመታ ማነስ ምክንያት ያቀረብነው ቅሬታ ምላሽ በማግኘቱ ተደስተናል.....የሰቆጣ ከተማ ነዋሪዎች

69

ሰቆጣ የካቲት 16/2011 በዋግኽምራ ብሔረሰብ አስተዳደር ዞን ከብልባላ እስከ ሰቆጣ ለሚገነባው የአስፓልት መንገድ ከአካባቢያቸው የሚነሱ የሰቆጣ ከተማ ነዋሪዎች በካሳ ግመታ ማነስ ምክንያት ያቀረቡት ቅሬታ ምላሽ በማግኘቱ መደሰታቸውን ገለፁ፡፡

በመንገድ ግንባታ ፕሮጀክቱ ለቅሬታ ተዳርገው የነበሩ 223 የልማት ተነሽዎችን ጥያቄ በመነጋገርና በመግባባት መፍታት እንደተቻለም ተገልጿል፡፡

በከተማው የቀበሌ 01 ነዋሪ ሊቀ ሂሩያን ማሪቆስ መራዊ ለኢዜአ እንደገለጹት በ2010 ዓ.ም የተደረገው የካሳ ግመታ ባለይዞታውን አማክሎ ባለመሰራቱ ቅሬታ ውስጥ መቆየታቸውን አስታውሰዋል፡፡

ለቅሬታው ምንጭም በግመታ መካተት የነበረባቸው ንብረቶች ታሳቢ ባለመሆናቸው በካሳ ክፍያው ሳይስማሙ ችግሩን በመነጋገር እንዲፈታ ተደጋጋሚ ቅሬታ ሲያቀርቡ እንደነበር ገልፀዋል፡፡

"በአሁኑ ወቅት ቅሬታችን ሰሚ አግኝቶ የልማት ተነሽዎችን ባማከለ መልኩ ባለይዞታው ባለበት እንዲለካ በመደረጉ ግልጽነት ያለው ስራ እንዲሰራ ተደርጓል" ብለዋል፡፡

የልማት ተነሽው መልሶ ሊቋቋምበት በሚችልበት መልኩ ግምት መውጣቱ ደግሞ ከእዚህ ቀደም ያነሱት የነበረውን ቅሬታ በአግባቡ ምላሽ እንዲያገኝ ማድረጉን ገልጸዋል፡፡

"ካሁን ቀደም የነበረው የካሳ ግመታ የልማት ተነሺው ራሱን መልሶ ሊያቋቁምበት በሚችልበት ምልኩ የተሰራ ባለመሆኑ ቅሬታን ስናቀርብ ቆይተናል" ያሉት ደግሞ ሃምሳ አለቃ መኮንን እጅጉ ናቸው፡፡

"በከተማዋ የሚከናወኑ የልማት ሥራዎችን ብንደግፍም የልማት ተነሺዎች ንብረት በአግባቡ አለመለካትና የወቅቱን የገበያ ዋጋ መሰረት ያላደረገ ግመታ በመሰጠቱ ስናነሳ የነበረው ቅሬታ አሁን ላይ ምላሽ አግኝቷል" ብለዋል፡፡

አቶ ዝናው አማረ የተባሉ ነዋሪ በበኩላቸው ለህብረተሰቡ ቅሬታ የሚመለከታቸው አካላት ምላሽ እንዲሰጡ ኮሚቴ በማዋቀር ሲጠይቁ መቆየታቸውን ገልጸዋል፡፡

"በዚህም ከህብረተሰቡ ጋር በመሆን ግልጽነት ባለው መልኩ ኮሚቴ ተቋቁሞ በመሰራቱ ቅሬታችን ተገቢ ምላሽ ሊያገኝ ችሏል" ብለዋል፡፡

በሰቆጣ ከተማ አስተዳደር የከተማ አገልግሎት ጽ/ቤት ኃላፊና በአስፓልት ሥራው የገማች ኮሚቴ ሰብሳቢ የሆኑት አቶ ጥጋቡ ሽመላሽ በበኩላቸው ከነዋሪዎች ሲነሳ የነበረው ቅሬታ አግባብ መሆኑን አስታውሰዋል።

ቀደም ሲል በነበረው ግመታ "መካተት የሚገባቸው ንብረቶች አልተካተቱም፣ የቤቶች ደረጃ ወጥ አለመሆንና የቤቶች ልኬታ ከወቅቱ ገበያ ጋር የሚጣጣም አይደለም" የሚሉ ቅሬታዎች በልማት ተነሽዎች ሲነሱ እንደነበር አስታውሰዋል፡፡

ይህም በከተማ አስተዳደሩ ከፍተኛ የመልካም አስተዳደር ችግር ሆኖ መቆየቱን ነው የገለጹት፡፡

የተነሺዎችን ቅሬታ በመቀበልም ከነሐሴ ወር 2010 ዓ.ም ጀምሮ ህብረተሰቡን ያመከለና ከመንገዶች ባለስልጣን ባለሙያዎች በተሳተፉበት ዳግም ግመታው እንዲጠና መደረጉን ተናግረዋል፡፡

"በዚህም በከተማዋ የሚገኙ 223 ባለይዞታዎች አሉን ያሉትን ንብረቶች በአግባቡ በመለካት ወቅታዊ  ዋጋን መሰረት ያደረገ ልኬታ በመስራት የልማት ተነሺዎችን ቅሬታ በመግባባት መፍታት ተችሏል" ብለዋል፡፡

የልማት ተነሺዎቹ መልሰው የሚቋቋሙበት መሬት ተዘጋጅቶላቸዋል ያሉት ኃላፊው ሌሎች መሰረተ ልማቶችን ለሟሟላትም ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በጋራ እንደሚሰራ ተናግረዋል፡፡

የብልባላ-ሰቆጣ የአስፓልት መንገድ ስራ ፕሮጀክት 98 ኪሎ ሜትር ርዝመት የሚኖረው ሲሆን በ2 ነጥብ 4 ቢሊዮን ብር ወጪ እየተገነባ ነው፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም