በኦሮሚያ ሞዴል አርሶ አደሮች ለውጤት የበቁበትን ልምድ ለማስፋፋት መረባረብ እንደሚያስፈልግ ተገለጸ

67

አዳማ የካቲት 16/2011 በኦሮሚያ ሞዴል አርሶ አደሮች ለውጤት የበቁበትን ልምድ በማስፋፋት ስኬቱ የጋራ እንዲሆን መረባረብ እንደሚያስፈልግ በክልሉ ምክትል ፕሬዝደንት ማዕረግ የግብርናና ገጠር ሴክተሮች ክላስተር አስተባባሪ ዶክተር ግርማ አመንቴ ገለጹ፡፡

በአዳማ ከተማ ነገ  የሚጠበቀው የኦሮሚያ ሞዴል አርሶ አደሮች የሽልማት ፕሮግራም ምክንያት በማድረግ ቀጣዩን የበልግና መኽር አዝመራ ውጤታማ ማድረግ በሚቻልበት ዙሪያ የፓናል ውይይት ተካሄዷል።

በውይይቱ ወቅት በክልሉ ምክትል ፕሬዝደንት ማዕረግ የግብርናና ገጠር ሴክተሮች ክላስተር አስተባባሪ ዶክተር ግርማ አመንቴ እንዳሉት የክልሉ አርሶ አደሮች በእቅድ የሰብል ልማቱን እንዲመሩ በማስቻል የግብርና ምርትና ምርታማነት እድገት ለመጨመር እየተሰራ ነው፡፡

ሞዴል አርሶ አደሮች ለውጤት የበቁበትን በተለይም ምርጥ ዘር፣ ማዳበሪያና በሌሎችም ግብዓቶች አጠቃቀም ላይ ያላቸው ልምድ በማስፋፋት ስኬቱ የጋራ እንዲሆን በቅንጅት መረባረብ ያስፈልጋል።

ቀጣይ የበልግና የመኽር አዝመራ ውጤታማ ለማድረግ በየደረጃው የሚገኙ አመራሮች በግብርና ግብዓት፣ በኤክስቴሽን አገልግሎትና ቴክኖሎጂ አጠቃቀም ላይ እውቀትና ክህሎት ይዘው  አርሶ አደሩ ማገዝ ይጠበቅባቸዋል፡፡

በዚህ ዙሪያ አመራሮች ያለባቸውን ክፍተት ለማስተካከል የሚያስችል ግንዛቤ የማስጨበጥ ሥራ እየተካሄደ መሆኑን ዶክተር ግርማ ተናግረዋል፡፡

" ለ2011/2012 የምርት ዘመን ሞዴል አርሶ አደሮች ዘንድ የተሟላ የኤክስቴሽንና የመካናይዜሽን አገልግሎት ተደራሽ ለማድረግ ግብ አስቀምጠን ርብርብ እያደረግ ነው" ብለዋል።

በዋናነት መንግስት የመካናይዜሽን አገልግሎቱን በሁሉም አርሶ አደሮች ዘንድ ተደራሽ ለማድረግ ጥረት እያደረገ መሆኑን ተናግረዋል።

በተያዘው ዓመት ወደ ባለሀብትነት የተሸጋገሩ 50 ሞዴል አርሶ አደሮችን ጨምሮ በአግሮፕሮሰሲንግና የግብርና መካናይዜሽን አገልግሎት ላይ እንዲሰማሩ መንግስት ዘላቂ ድጋፍ እንደሚያደርግ አስታውቀዋል።

በፓናል ውይይቱ ጽሁፍ ያቀረቡት የግብርና ትራንስፎርሜሽን ኤጄንሲ ተወካይ ዶክተር ጨመዶ ሃጫሉ በበኩላቸው በሀገሪቱ  የሰብል ልማት ቴክኖሎጂ  አጠቃቀም 15 በመቶ  ብቻ እንደሆኑ ገልጸዋል፡፡

አሁን ያለውን የግብርና ምርትና ምርታማነት እድገት  ለመጨመር የምርጥ ዘር፣የተፈጥሮና የኬሚካል ማዳበሪያ አጠቃቀም ወደ 30 በመቶ ማሳደግ እንደሚገባ አመልክተዋል።

ለዚህም አርሶ አደሩ በአመለካከት፣በአስተሳሰብና በተግባር ማብቃትና በቂ የቴክኖሎጂ አቅርቦት ማስፋት ላይ በሙሉ አቅም መስራት እንደሚገባ ጠቁመዋል።

" በመንግስት፣በግሉ ባለሀብትና በአርሶ አደሮች ማሳ ጭምር በማህበር ተደራጀተው ምርጥ ዘር ብዜት ላይ በቅንጅት መስራት አለብን " ብለዋል፡፡

የኬሚካል ማዳበሪያ በሀገር ውስጥ የሚመረቱበት ሁኔታዎች ማመቻቸት ላይ አሁንም ትኩረት እንደሚያስፈልግም ጠቅሰዋል።

በአዳማ ከተማ ነገ  በሚካሄድ  ስነስርዓት ሞዴል የሆኑ 716 አርሶና አርብቶ አደሮች፣የግብርና ምርምር ማዕከላትና ሌሎች በግብርና ውስጥ ጉልህ አስተዋጽኦ ያበረከቱ ተቋማት  እንደሚሸለሙ ይጠበቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም