የተሽከርካሪ አጠቃቀምን አስመልክቶ በሚኒስትሮች ምክር ቤት የወጣው መመሪያ እየተተገበረ አይደለም

438

አዲስ አበባ የካቲት 16/2011 የመንግሥት ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎችን የተሽከርካሪ አጠቃቀም አስመልክቶ የሚኒስትሮች ምክር ቤት ያወጣው መመሪያ በበርካታ ተቋማት እየተተገበረ አለመሆኑን የገንዘብ ሚኒስቴር አስታወቀ።

የሚኒስትሮች ምክር ቤት ሐምሌ 28 ቀን በ2009 ዓ.ም ሚኒስትሮች፣ሚኒስትር ዴኤታዎችና፣ በተለያዩ ተቋማት በየደረጃው የሚገኙ የስራ ኃላፊዎችን የተሽከርካሪ አጠቃቀም የተመለከተ መመሪያ ማውጣቱ ይታወቃል።

በመመሪያው ቁጥር 4 ንዑስ ቁጥር 1 ከፍተኛ የመንግስት የሥራ ኃላፊዎች ወጪ ቆጣቢና ውጤታማ የፋይናንስ አጠቃቀም እንዲኖር ለከተማ ውስጥ ስራ አውቶሞቢል ተሽከርካሪዎችን እንዲጠቀሙ ተደንግጓል።

በዚህ መሰረት የሥራ ኃላፊዎቹ ስቴሽን ዋገን ቪ 8፣ ቪ 9፣ ፕራዶና ፓጃሮ ተሽከርካሪዎችን ከሚጠቀሙ ይልቅ አውቶሞቢል ተሽከርካሪዎችን ቢጠቀሙ ከፍተኛ ወጪ በመቀነስ ውጤታማ አገልግሎት መስጠት እንደሚቻል ሚኒስቴሩ ገልጿል።

አውቶሞቢል ተሽከርካሪዎቹን በሥራ ላይ ማዋል ያስፈለገው ወጪ ቆጣቢና ውጤታማ የፋይናንስ አጠቃቀም ለማስፈን ቢሆንም የሥራ ኃላፊዎቹ ተግባራዊ እያደረጉት አለመሆኑን ጠቁሟል።

የሚኒስቴሩ የህዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር አቶ ሃጂ ኢብሳ እንዳሉት በሚኒስትሮች ምክር ቤት በወጣው መመሪያ መሠረት ለመንግስት ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች የተመደቡት አውቶሞቢል ተሽከርካሪዎች ለከተማ ሥራ ሲውሉ አይታይም።

በርካታ የመንግስት የሥራ ኃላፊዎች አዲስ የተመደቡላቸውን ተሽከርካሪዎች በማቆም አሁንም ስቴሽን ዋገን ቪ 8፣ ቪ 9፣ ፕራዶና ፓጃሮ ተሽከርካሪዎችን ከተማ ውስጥ ሲጠቀሙ ይስተዋላሉ ነው ያሉት።

በመመሪያው በሁሉም የመንግስት ተቋማት የሚገኙ ስቴሽን ዋገን ቪ 8፣ ቪ 9፣ ፕራዶና ፓጃሮ ተሽከርካሪዎች ለመስክ ሥራ ብቻ እንዲውሉና በአንድ ማዕከል ተሰብስበው እንዲቀመጡ መወሰኑን አቶ ሀጂ አስታውሰዋል።

ሆኖም ካለው የተሽከርካሪ ማቆሚያ እጥረትና ለአሰራርም አመቺ ባለመሆኑ ተሽከርካሪዎቹን በአንድ ማዕከል የማሰባሰቡም ስራ ተግባራዊ አለመሆኑን ገልጸዋል።

መንግስት ከ350 ሚሊዮን ብር በላይ በማውጣት 400 አውቶሞቢል ተሽከርካሪዎችን ገዝቶ እስከ ጥር 2011 ዓ.ም አጋማሽ 397ቱን ለፌዴራል መስሪያ ቤቶች የሥራ ኃላፊዎች ማከፋፈሉንም ተናግረዋል። 

የገንዘብ ሚኒስቴርም የተሽከርካሪዎቹን አጠቃቀም በተመለከተ ለፌዴራል መስሪያ ቤቶች የሥራ ኃላፊዎች ከየካቲት 1 ቀን 2011 ዓ.ም ጀምሮ ተግባራዊ እንዲያደርጉ ደብዳቤ መላኩን ጠቁመዋል።

በየመስሪያ ቤቶቹ የሚገኙ የውስጥ ኦዲተሮች የሥራ ኃላፊዎች በሚኒስትሮች ምክር ቤት የወጣውን መመሪያ በሥራ ላይ ማዋል አለማዋላቸውን ከነምክንያቱ በማጣራት ለሚኒስቴሩ ሪፖርት በማድረግ የተጣለባቸውን ኃላፊነት እንዲወጡም አቶ ሀጂ ጥሪ አቅርበዋል።

ከየመስሪያ ቤቶቹ የሚቀርበው ሪፖርት በተያዘው ወር መጨረሻ ተገምግሞ የሚኒስትሮች ምክር ቤት ውሳኔ እንዲሰጥበት ይደረጋል ሲሉም አክለዋል።

አንድ ቪ 8 ተሽከርካሪ ለመግዛት 5 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር የሚጠይቅ ሲሆን ይህም ከአንድ አውቶሞቢል ጋር ሲነጻጸር የአምስት እጥፍ ጭማሪ አለው። 

ቪ 8 ተሽከርካሪ በአንድ ሊትር  ነዳጅ  7 ኪሎ ሜትር ሲጓዝ በአንጻሩ አውቶሞቢል ተሽከርካሪ በተመሳሳይ የነዳጅ ፍጆታ እስከ 13 ኪሎ ሜትር ይጓዛል። የአውቶሞቢል የጥገና ወጪም ከቪ 8 ቅናሽ ያለው ነው።   

50 ባለ 2 ሺህ የፈረስ ጉልበት ተሽከርካሪዎች ለሚኒስትሮች፣ 110 ባለ 1 ሺህ 800 የፈረስ ጉልበት ለሚኒስትር ዴኤታዎችና 1 ሺህ 600  የፈረስ ጉልበት ያላቸው 240  አውቶሞቢል ተሽከርካሪዎች ለዋና ዳሬክተሮችና ለምክትል ዋና ዳሬክተሮች መመደባቸውን ከገንዘብ ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም