ኮርፖሬሽኑ ግዙፍ የልማት ፕሮጀክቶችን በማካሄድ ላይ መሆኑን ገለጸ

64

አዳማ የካቲት 15/2011 የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ሥራዎች ኮርፖሬሽን በግንባታው ዘርፍ  ግዙፍ የልማት ፕሮጀክቶችን በማካሄድ ላይ መሆኑን ገለጸ።

ኮርፖሬሽኑ የ2011 በጀት ዓመት የመጀመሪያ ስድስት ወራት የእቅድ አፈጻጸም ጉባኤ ዛሬ በአዳማ ከተማ  ጀምሯል፡፡

በዚህ ወቅት የኮርፖሬሽኑ ዋና ስራ አስፈፃሚ  ኢንጅነር ኃይለመስቀል ተፈራ እንዳሉት መስሪያ ቤታቸው እያካሄዳቸው ካሉት ግዙፍ ፕሮጀክቶች መካከል የትራንስፖርት፣ ኮንስትራክሽን፣የመጠጥ ውሃ፣ግድብና መስኖ መሰረተ ልማት ይገኙበታል።

እነዚህ የልማት ፕሮጀክቶች የሚያካሄዱት በተለይ የግሉ ዘርፍ በማይደርስባቸው አካባቢዎች  በመግባት የገበያ ጉድለቱን ለመሙላት እንደሆነ ተናግረዋል፡፡

በበጀት ዓመቱ የመጀመሪያዎቹ ስድስት ወራት ኮርፖሬሽኑ ባደረገው እንቅስቃሴ በአንድ ቢሊዮን 700 ሚሊዮን  ብር ወጪ የመንገድ ግንባታና ጥገና፣ በውሃ ሀብት ልማትና ህንጻ ግንባታዎች መካሄዳቸውን ጠቅሰዋል።

የመንገድ ስራው የ40 ኪሎ ሜትር አዲስ ግንባታና የ2 ሺህ 170 ኪሎ ሜትር ጥገና  መሆኑን አመላክተዋል።

የተለያዩ የመስኖ፣ የግድብ፣የንጹህ መጠጥ ውሃ እንዲሁም በደረቅ ወደብ ፕሮጀክቶች  አፈጻጸም ከእቅዱ  27 ነጥብ 28 በመቶ ላይ  እንደሚገኝ ጠቁመዋል።

በተለይ ከመስኖ ፕሮጀክቶች ውስጥ   የኦሞ ኩራዝ፣አርጆ ደዴሳና ወልቃይት የግድብና መስኖ  ጠቅሰዋል።

በአሁኑ ወቅትም ኮርፖሬሽኑ ለሀገር ምጣኔ ሀብት እድገት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያላቸው የኤርፖርት፣ የወደብ፣ የኃይድሮ ኤሌክትሪክ ኃይልና  ሌሎችም  ስራዎች ላይ መሰማራቱን ዋና ስራ አስፈጻሚው አብራርተዋል።

በኮርፓሬሽኑ የሀብት አስተዳደርና ሰርቪስ ዘርፍ ምክትል ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ አመንቴ ዳዲ በበኩላቸው በኮርፖሬሽኑ የሚካሄዱ ፕሮጀክቶችን ለማቀላጠፍ 670 ሚሊዮን ብር በሆነ ወጪ 198 የግንባታ  መሳሪያዎች ግዥ በመፈጸም  ስራ ላይ እንዲውሉ መከፋፈላቸውን አስታውቀዋል፡፡

ባለፉት ስድስት ወራት ኮርፖሬሽኑ ከገነባቸው  ፕሮጀክቶች ከ469 ሚሊዮን ብር ያልተጠራ ትርፍ ማግኘቱም  ተመልክቷል፡፡

ለሶስት ቀናት በሚቆየው ጉባኤው በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የገቢ በጀትና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አባላትና ሌሎችም ባለድርሻ አካላት እየተሳተፉ ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም