በአሶሳ ዩኒቨርሲቲ ግጭት በተማሪዎች ሞት የተጠረጠረው ግለሰብ በዋስ እንዲለቀቅ መወሰኑ እንዳሳዘናቸው ነዋሪዎች ገለጹ

52

አሶሳ የካቲት 15/2011በአሶሳ ዩኒቨርሲቲ  ከሦስት ወራት በፊት በተከሰተ ግጭት በሶስት ተማሪዎች ሞት የተጠረጠረው ግለሰብ በዋስ እንዲለቀቅ መወሰኑ አግባብነት እንደሌለው የአሶሳ ከተማ አንዳንድ ነዋሪዎች ገለጹ።

የፌደራልና የቤኒሻንጉል  ጉምዝ ክልል ፖሊስ ኮሚሽኖች የተጠርጣሪውን ዋስትና በመቃወም ያቀረቡት ይግባኝ ተቀባይነት አግኝቷል፡፡

ከነዋሪዎቹ  አንዳንዶቹ  ለኢዜአ እንዳሉት በዩኒቨርሲቲው በተከሰተ ግጭት በተማሪዎች ሞት ተጠያቂ  ነው የተባለው ግለሰብ በቁጥጥር ሥር ውሎ ጉዳዩ በሕግ መታየቱ የሚያበረታታ ነው፡፡

ሆኖም ግለሰቡ ትናንት በዋስትና ከእስር መፈታቱ ግን  አሳዝኖናል ብለዋል።

በግድያ ወንጀል የተጠረጠረ ግለሰብ በዚህ መልኩ መለቀቁ አግባብ እንዳልሆነም  ተናግረዋል፡፡

''ተጠርጣሪው በአገሪቱ የታየው ህዝባዊ ለውጥ ለማደናቀፍ ከሚሯሯጡ ሃይሎች ጋር ግንኙነት አለው'' የሚል እምነት እንዳላቸው ነዋሪዎቹ ገልጸዋል፡፡

የአሶሳ ወረዳ ፍርድ ቤት ተወካይ አቶ አንበሳ ዋጅራ ተከሳሹ ከተያዘበት ህዳር 16 /2011 ጀምሮ እስከ ትናንት በጊዜ ቀጠሮ ለዘጠኝ ጊዜ ፍርድ ቤት መቅረቡን ያስረዳሉ፡፡

ፖሊስ በግለሰቡ ላይ ያቀረበው ማስረጃ ወንጀሉን መፈጸሙን ስለማያመለክት ፍርድ ቤቱ አምስት ሺህ ብር በዋስትና በማስያዝ ጉዳዩን ከማረሚያ ቤት ውጭ ሆኖ እንዲከታተል መወሰኑን ገልጸዋል፡፡

ግለሰቡ የተጠረጠረው በዩኒቨርሲቲው የተማሪዎች ሞት ብቻ ሳይሆን፤ በሰኔ 2011 በአሶሳ ከተማ በተከሰተው ሁከት ጭምር እንደሆነም አመልክተዋል፡፡

ግለሰቡ የተጠረጠረበት ወንጀል ከባድ በመሆኑ ፍርድ ቤቱ ጉዳዩን የማየት ስልጣን ባይኖረውም፤በጊዜ ቀጠሮ ላይ የሚገኝና ክስ ያልተመሰረተበትን  ጉዳይ የማየት ሥልጣን ስላለው ጉዳዩን እንደተመለከተው አስረድተዋል፡፡

የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር ኮማንደር አዳሙ እጀታ  እንደተናገሩት የክልሉና የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽኖች ያቋቋሙት የምርመራ ቡድን የፍርድ ቤት ውሳኔ ተቃውመውታል፡፡

ምርመራው እስኪጠናቀቅ ድረስ ተጠርጣሪው በማረሚያ ቤት እንዲቆይ ያቀረቡት ይግባኝ ተቀባይነት አግኝቷል ብለዋል፡፡

ግለሰቡ በወንጀሉ ተጠርጥሮ በቁጥጥር ሥር በዋለበት ወቅት “ታምሜያለሁ” የሚል ሐሰተኛ ምክንያት ለፖሊስ በማቅረብ መድኃኒት ለመውሰድ ወደ መኖሪያ ቤቱ አጅበውት በሄዱት የጸጥታ ሃይሎች ላይ ጠመንጃ በማውጣት ማስፈራራቱ ይታወሳል፡፡

በአሶሳ ከተማ 2010 እና  ዘንድሮ በአሶሳ ዩኒቨርሲቲ በተከሰተው ግጭት  ከ18 በላይ ሰዎች ሕይወት አልፏል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም