የጤና አገልግሎት ጥራት ችግርን ለማስወገድ እርምጃ እየተወሰደ ነው-- የጤና ሚኒስትር

111

አዲስአበባ የካቲት 15/2011 በኢትዮጵያ የጤና አገልግሎት ጥራት ችግርን ለመቆጣጠርና ለማስወገድ የሚያስችል እርምጃ እየተወሰደ መሆኑን የጤና ሚኒስትሩ ዶክተር አሚር አማን ገለፁ።  

ሚኒስትሩ ይህንን የገለፁት የኢትዮጵያ ህክምና ማህበር 55ኛ ዓመታዊ ጉባኤ ዛሬ አዲስ አበባ ውስጥ ሲጀመር ባደረጉት ንግግር ነው።

በአገሪቱ የጤና አገልግሎት ተደራሽነትን ለማጠናከር በርካታ ውጤታማ ተግባራት የተከናወኑ ቢሆንም ከዘርፉ የአገልግሎት ጥራት ጋር በተያያዘ ግን ከፍተኛ ክፍተት አለ ብለዋል።

ለአብነትም ባለፉት ዓመታት ከተሰሩት የጤና ተቋማት መካከል 40 በመቶ የሚሆኑት የኤሌክትሪክና የውሃ አቅርቦት በተገቢው መጠንና ጥራት እንዳልተሟላላቸው ተናግረዋል።

መንግስት ይህንን ችግር በመፍታት የጤና ተቋማቱ ጥራት ያለው አገልግሎት መስጠት ይችሉ ዘንድ ከተለያዩ የሚመለከታቸው አካላት ጋር በቅንጅት እየሰራ መሆኑንም አንስተዋል።

ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር በተደረሰው ስምምነት መሰረትም እስከ 2012 ዓ.ም መጨረሻ ድረስ ሁሉም ጤና ጣቢያዎች የኤሌክትሪክና የውሃ አገልግሎት ተጠቃሚ እንዲሆኑ ትኩረት ተደርጎ እየተሰራ መሆኑን ሚኒስትሩ አስታውቀዋል።

በሌላ በኩል ዩኒቨርስቲዎች የሚቀበሉት የህክምና ተማሪ ቁጥር መብዛትም  ከጥራት ጋር በተያያዘ ከሚነሱት ችግሮች መካከል መሆኑንም ዶክተር አሚር ጠቅሰዋል። 

በተያዘው ዓመት ግን በህክምና የሚሰለጥኑት ሙያተኞች ጥራትን ለማሻሻል እንዲያግዝ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የሚቀበሏቸውን ተማሪዎች ቁጥር በግማሽ እንዲቀንሱ ተደርጓል።

በቀጣይም የህክምና ተማሪዎችን የመቀበል አቅም ያላቸው ዩኒቨርስቲዎች ብቻ እንዲቀበሉ፣ የሚፈለገውን ደረጃ ጠብቀው በትክክል የማያስተምሩትን ደግሞ ደረጃቸውን ዝቅ የማድረግ እርምጃ እንደሚወሰድም የጤና ሚኒስትሩ አስታውቀዋል።

መንግስት የህክምና ትምህርት የሚሰጡ ከፍተኛ ተቋማትን የማሰልጠን አቅም ለማሳደግ የሚያደርገውን ድጋፍ ይቀጥላል ያሉት ዶክተር አሚር ድጋፍ ተሰጥቷቸውም መሻሻል የማያሳዩ ከሆነ ግን የህክምና ትምህርቱ እንዲዘጋ የእግድ እርምጃ እንደሚወሰድ አስጠንቅቀዋል።                                                                        

የኢትዮጵያ ህክምና ማህበር ፕሬዝዳንት ዶክተር ገመቺስ ማሞ ጥራት የህክምና መሰረት በመሆኑ የዘርፉ ትምህርት ተቋማት ምንም ግብአትና የሰው ሃይል ሳይኖራቸው ብዙ ተማሪ ከመቀበል መቆጠብ እንዳለባቸው አሳስበዋል።

የህክምና ማህበሩ የዘርፉን ትምህርትና አገልግሎት ጥራት ለማሻሻል በሚያስችሉ መስኮች የማማከርና ሌሎች ድጋፎችን ለማቅረብ ከጤና ሚኒስቴር ጋር እንደሚሰራ ገልፀዋል።

የማህበሩ አባላት "ሁሉን አቀፍ የጤና አገልግሎት ተደራሽነት በኢትዮጵያ" በሚል እስከ እሁድ በሚያካሄዱት ጉባኤ ማህበሩንና ሙያውን ማጠናከር በሚያስችሉ የተለያዩ ጉዳዮች ላይ ይመክራሉ።

በኢትዮጵያ የመጀመሪያ የሙያ ማህበር እንደሆነ የሚነገርለት የኢትዮጵያ ህክምና ማህበር በአሁኑ ወቅት በተለያየ የህክምና ዘርፍ የተሰማሩ 4 ሺህ ያህል አባላት አሉት።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም