በሶማሌ ክልል ተከስቶ በነበረው ችግር ሳቢያ ከሁለት ሺህ በላይ ተሽከርካሪዎች በሕገ ወጥ መንገድ አገር ውስጥ ገብተዋል

80

ጅግጅጋ የካቲት 15/2011 በሶማሌ ክልል ተከስቶ በነበረው የፀጥታ ችግር ሳቢያ ከሁለት ሺህ በላይ ተሽከርካሪዎች ቀረጥና ታክስ ሳይከፈልባቸው አገር ውስጥ  መግባታቸውን በገቢዎች ሚኒስቴር የጅግጅጋ ቅርንጫፍ  ጽህፈት ቤት ገለጸ።

የቅርንጫፍ ጽህፈት ቤቱ ኃላፊ አቶ ደመላሽ ተሾመ ለኢ ዜ አ እንደገለጹት በክልሉ ባለፈው ዓመት መጨረሻ በተከሰተው ግጭት በሕገ ወጥ መንገድ የገቡት የቤትና የጭነት ተሽከርካሪዎች እንዲሁም ባለሦስት እግር ባጃጆች ናቸው።

ተሽከርካሪዎቹ ወደ አገር ውስጥ የገቡት በዶሎ ቆራሃይ፣በጀረርና ፋፈን ዞኖች በተፈጠረው ክፍተት ተጠቅመው ነው።

ለአብነትም "በቀብሪደሃር ከተማ 200 ባጃጆችና ሌሎች ተሽከርካሪዎች ገብተዋል፤ በቀብሪ በያህ ከተማ ደግሞ 34 መኪናዎች ናቸው የገቡት" ሲሉም ተናግረዋል።

በክልሉ በተከሰተው ግጭት በጉምሩክ መቆጣጠሪያ ጣቢያዎች በሕገ ወጥ መንገድ የገቡና ግምታቸው 20 ሚሊዮን ብር የሆኑ 40 ተሽከርካሪዎች እንደተዘረፉ ኃላፊው ገልጸዋል።

በክልሉ የተዘጉትን የጉምሩክ ጣቢያዎችን እንደገና ለመክፈት ሳይቻል መቆየቱንም ተናግረዋል።

በክልሉ በኩል በሚከናወነው የወጪና ገቢ ንግድ እንቅስቃሴ ሕግን የተከተለ ለማድረግ ሚኒስቴሩ ከክልሉ መንግሥት አመራር ጋር እየተወያየ መሆኑንም አስታውቀዋል ።

የክልሉ ንግድ፣ ትራንስፖርትና ኢንዱስትሪ ቢሮ ኃላፊ አቶ አብዲራህማን መሐመድ በፀጥታ ችግር ምክንያት ወደ ክልሉ የገቡ ተሽከርካሪዎችን ወደ ሕጋዊ መሥመር ለማስገባት ከክልሉና ከፌዴራል መንግሥት የተውጣጡ አካላት በቅርቡ እንደሚሰማሩ ተናግረዋል።

በሶማሌ ክልል ቀደም ሲል 12 የጉምሩክ መቆጣጠሪያ ጣቢያዎች በሥራ ላይ የነበሩ ሲሆን፣አሁን በሥራ ላይ የሚገኙት ግን የቶጎ ውጫሌና የአውበሬ ጣቢያዎች ብቻ ናቸው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም