''የአገልግሎቶች ጽህፈት ቤት አገልግሎት አልሰጠንም''-የወላይታ ሶዶ ከተማ ነዋሪዎች

95

ሶዶ የካቲት 15/2011 የወላይታ ሶዶ ከተማ ማዘጋጃ ቤታዊ አገልግሎቶች ጽህፈት ቤት አገልግሎት አሰጣጥ ለእንግልት እንደዳረጋቸው ነዋሪዎች ተናገሩ፡፡

ተቋሙ በበኩሉ የአገልግሎት አሰጣጥ ማሻሻያ ስታንዳርድ ማዘጋጀቱንና  ችግር ባለባቸው ሠራተኞቹ ላይ እርምጃዎች ወስጄያለሁ ይላል፡፡

የከተማው አንዳንድ ነዋሪዎች ለኢዜአ እንደተናገሩት ጽህፈት ቤቱ የሚሰጠው አገልግሎት ከተቋቋመበት ተግባር አኳያ ጋር  የማይጣጣምና  በአፋጣኝም  መስተካከል የሚገባው ሆኖ አግኝተውታል።

ከአስተያየት ሰጪዎቹ አቶ አየለ ሳና  በጽህፈት ቤተ  የቀጠሮ መብዛትና መጉላላት እንደሚገጥማቸው ተናግረዋል፡፡

በመሬት አስተዳደር ዘርፍ  የተመደቡ ባለሙያዎች ባለጉዳይን ከማመናጨቅ ጀምሮ ለሙስናና ኪራይ ሰብሳቢነት የተጋለጡ ናቸው ብለዋል፡፡

ጽህፈት ቤተ የሕዝብ መድረኮች ማዘጋጀቱ ተስፋ ሰጪ ቢሆንም፤ አስተያየቶችን ወደ ተግባር በመቀየር አገልግሎቱን ማስተካከል እንደሚገባውም ገልጸዋል፡፡

በልማት ምክንያት ተነሺ ተብለዉ ከአምስት ዓመታት በላይ ምላሽ ለማግኘት ወደ ጽህፈት ቤቱ መመላለሳቸውን የተናገሩት ደግሞ የድል በትግል ቀበሌ ነዋሪዋ ወይዘሮ አየለች አመጣ ናቸው፡፡

''ተለዋጭም ሆነ ተገቢ ግምት ሳይሰጠኝ መጉላላቴ ተገቢ አይደለም። ለማዘጋጃ ቤቱም ሆነ በየመድረኩ ችግሬን ባነሳ ሰሚ አጥቻለሁ'' ሲሉም  ቅሬታቸውን ተናግረዋል፡፡

የሰላም ቀበሌ ነዋሪ የመቶ አለቃ ኢያሱ አይዴ በበኩላቸው በጽህፈት ቤቱ ''የባለጉዳይ ቀን'' ተብሎ የተያዘ ጊዜ ቢኖርም፤ በዚያ መሠረት እያስተናገደን አይደለም ብለዋል፡፡

በስብሰባ ምክንያት አለመገኘት፤በቂ ምላሽ አለመስጠትና በአካል ተገኝቶ ምላሽ አለመስጠት የጽህፈት ቤቱ  መገለጫዎች መሆናቸውን አመልክተዋል።

የወላይታ ሶዶ ከተማ ማዘጋጃ ቤታዊ አገልግሎቶች ጽህፈት ቤት ዋና ሥራ አስኬያጅ አቶ ፍሬው ሻንካ ከነዋሪዎቹ የተነሱ ቅሬታዎች ትክክል መሆናቸው አምነዋል፡፡

የችግሩን ባለቤቶች በግለሰብ ደረጃ ለመለየት በከተማው ባሉ ክፍለ ከተሞች መድረኮች ተፈጥረው የሕዝብ አስተያየቶች መሰብሰባቸውን ተናግረዋል፡፡

በዚህም በመሬት አስተዳደርና በወጣቶች ሥራ ዕድል ፈጠራ ዘርፍ የሥነ-ምግባር ግድፈትና አገልግሎት አሰጣጥ ችግር ፈጥረዋል የተባሉ ስድስት ባለሙያዎች ከሥራ መታገዳቸውን አስታውቀዋል፡፡

በሕግ መታየት ያለባቸዉ ጉዳዮችም ክትትል እየተደረገባቸው መሆኑን ተናግረዋል፡፡

የነዋሪዎችን አስተያየት መነሻ ያደረገ የአገልግሎት አሰጣጥ ማሻሻያ ስታንዳርድ በመዘጋጀት ላይ እንደሚገኝም ገልጸዋል፡፡

በክፍለ-ከተሞችና በማዘጋጃ ቤቱ መካከል የተሳለጠ አገልግሎት የሚታየውን  የአሰራር ክፍተት ለመሙላት የባለሙያዎችን አቅም ለማሳደግ  እየተሰራ ነው ብለዋል፡፡

አገልግሎት አሰጣጡን በተፈለገዉ ልክ ለማሻሻል ሕዝቡ ተሳትፎው  እንዲያጠናክር  ጠይቀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም