በባሌ የተከሰተው የኩፍኝ በሽታን ለመከላከል ጥረት እየተደረገ ነው

63

ጎባ የካቲት 15/2011 በባሌ ዞን በተወሰኑ ወረዳዎች የተከሰተው የኩፍኝ በሽታ እንዳይስፋፋ ለመከላከል ጥረት እየተደረገ መሆኑን የዞኑ ጤና ጥበቃ ጽህፈት ቤት ገለፀ።

በሽታው በወረርሽኝ መልክ መከሰቱ ሪፖርት ከተደረገበት ዕለት ጀምሮ በሽታውን መከላከልና መቆጣጠር የሚያስችሉ ተግባራት እያተከናወኑ መሆኑን የጽህፈት ቤቱ ምክትል ኃላፊ አቶ እሸቱ ቶሎሳ ለኢዜአ ተናግረዋል፡፡

የበሽታው ቅኝትና ክትትል ሥራ በሌሎችም ወረዳዎች በተጠናከረ መልኩ መቀጠሉን  አስታውቋል።

ካለፈው ታህሳስ ወር መጨረሻ ጀምሮ ጊኒርና ሲናና ጨምሮ በተወሰኑ ወረዳዎች የተከሰተውን  ወረርሽኝ  ወደ ሌሎች የተቀሩት አካባቢዎች  እንዳይስፋፋ ለመከላከል ጥረት እየተደረገ ነው።

በማሳልና በማስነጠስ  ወቅት ከአፍና አፍንጫ በሚወጣ እርጥበት አማካኝነት ከሰው ወደ ሰው እንደሚተላለፍ ያመለከቱት የጽህፈት ቤቱ ምክትል ኃላፊ "በዞኑ በሽታው እንዲሠራጭ ያደረጉት አጋላጭ ሁኔታዎች መካከል ያልተከተቡ ህፃናት መኖራቸው ነው " ብለዋል።

እንዲሁም የመድኃኒት እጥረትና በበሽታው የተያዙ ሰዎችን ህብረተሰቡ በቤት ውስጥ በመደበቅ የተሳሳተ ዝንባሌ በሽታውን ለመቆጣጠር አስቸጋሪ ማድረጉን አስረድቷል፡፡

አቶ እሸቱ እንዳሉት በዞኑ እስካሁን ከ1ሺህ20 የሚሆኑ ሰዎች በበሽታው ተይዘው በጤና ተቋማት የህክምና እርዳታ አግኝተዋል፤  53 ሰዎች ደግሞ ተኝተው እየተካሙ ነው፡፡

ከወረርሽኙ ጋር ተያይዞ የአንድ ሰው ህይወት ማለፉን ጠቁመው ለመቆጣጠር ከመድኃኒት እጥረትና ተያያዥ ጉዳዮች ጋር ተያይዞ የሚታየውን ተግዳሮቶች ጉዳዩ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በቅንጅት እየተሰራበት መሆኑን አመልክተዋል፡፡ 

የፌዴራል ጤና ጥበቃ ሚኒስቴርን ጨምሮ ሌሎች መንግስታዊና መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ድጋፍ እያደረጉ እንደሚገኙ አስረድተዋል።

በመደበኛ መልኩ ወረርሽኙን ለመቆጣጠር ከሚደረገው ጥረት ባሻገር ከ844 ሺህ በላይ ለሚሆኑ ከዘጠኝ ወር እስከ 15 ዓመት ዕድሜ ክልል ለሚገኙ ህፃናት ወረርሽኙ በተከሰተባቸው ወረዳዎች ክትባት በዘመቻ መልክ ለመስጠት ቅድመ ዝግጅት እየተደረገ ነው።

አቶ እሸቱ ህብረተሰቡ የበሽታውን ምልክት በሚያይበት ወቅት ወደ ጤና ተቋማት በመሄድ በነፃ የሚሰጠውን የህክምና አገልግሎት ተጠቃሚ እንዲሆን መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡

የጊኒር ወረዳ  ነዋሪው አቶ አህመድ ሙክታር በሰጡት አስተያየት በበሽታው ተይዘው ወደ ህክምና ተቋማት ሲሄዱ መድኃኒት በወቅቱ  በማግኘት ላይ ክፍተት ስለሚስተዋል ሊስተካከል እንደሚገባ ጠቁመዋል፡፡

" ወረርሽኙን ለመከላከል በህብረተሰቡ ግንዛቤ ላይ በስፋት ሊሰራበት ይገባል"  ያሉት ደግሞ ሌላዋ የወረዳዋ ነዋሪ ወይዘሮ አልፍያ መሐመድ ናቸው፡፡ 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም