በዩኒቨርሲቲዎች የሳይንስና ቴክኖሎጂ ማዕከላትን ለመገንባት ስምምነት ተፈረመ

90

አዲስ አበባ  የካቲት 15/2011 የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር የተማሪዎችን የሳይንስና ቴክኖሎጂ አቅም ማሳደግ የሚያስችል ማዕከል ለመገንባት ስቲም ፓወር ከተሰኘ ተቋም ጋር ስምምነት ተፈራረመ።

ስቲም ፓወር የተሰኘው ተቋም ተማሪዎች በሳይንስ፣ ቴክኖሎጂ፣ በኢንጂነሪንግ እና ሂሳብ ትምህርቶች ብቁና ተወዳዳሪ እንዲሆኑ ከንድፈ-ሃሳብ ትምህርት በዘለለ በተግባር እንዲማሩ የሚያስችል ማዕከል በዩኒቨርሲቲዎች እየገነባ ነው።

ተቋሙ እንደ አውሮጳውያን አቆጣጠር በ1990ዎቹ በአሜሪካ የተመሰረተና ወደ ኢትዮጵያ ከመጣ 12 ዓመታትን ያስቆጠረ ሲሆን እስካሁን በኢትዮጵያ ባሉ የመንግስት ዩኒቨርሲቲዎች በሳይንስና ኢንጂነሪንግ ትምህርቶች ላይ በትብብር ሲሰራ ቆይቷል።

ከአሁን ቀደም 13 ማዕከላትን በዩኒቨርሲቲዎች ገንብቶ አገልግሎት እየሰጡ ሲሆን በተጨማሪ ሰባት ዩኒቨርሲቲዎች ለማስፋት ነው ከሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር እና ከዩኒቨርሲቲዎቹ ጋር የመግባቢያ ሰነድ የተፈራረመው።

ከተቋሙ ጋር ስምምነቱን የፈረሙት የአዲስ አበባ፣ አዲግራት፣ አርባ ምንጭ፣ ደብረ ብርሃን፣ ድሬድዋ ፣ጅማ እና ወሎ ዩኒቨርስቲዎች እንዲሁም የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ናቸው።

በአሜሪካና በኢትዮጵያ የተቋሙ ዋና ዳይሬክተር ወይዘሮ ቅድስት ገብረአምላክ ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት እንደገለፁት፤ ድርጅቱ በኢትዮጵያ ያሉ ተማሪዎች በሳይንስና ቴክኖሎጂ የተሻለ አቅም እንዲኖራቸው ከባለድርሻ አካላት ጋር እየሰራ ነው።

ተቋሙ በአገሪቱ የሚገነባቸው ማዕከላት ለዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ብቻ ሳይሆን ለሁለተኛ ደረጃ ተማሪዎችም ጠቀሜታቸው የጎላ መሆኑን ነው የሚናገሩት።

የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስትር ዴኤታ ፕሮፌሰር አፈወርቅ ካሱ በበኩላቸው፤ ኢትዮጵያ እያሳየች ያለውን ፈጣን እድገት ቀጣይነት ለማረጋገጥ የፈጠራ ሥራዎች አስፈላጊ በመሆናቸው የማዕከላቱ ግንባታ ከፍተኛ አስተዋጽኦ አለው ብለዋል።

ተማሪዎች በንድፈ-ሃሳብ የሚማሩትን በተግባር ለመሞከር የሚያግዝና ተማሪዎች አቅማቸውን እንዲያወጡ የሚረዳም ነው ይላሉ።

የማዕከላቱ ግንባታ ሳይንሳዊ አስተሳሰብን በማህበረሰብ ውስጥ ለማስረጽ አይነተኛ ሚና እንደሚኖረውም ሚኒስትር ዴኤታው ተናግረዋል።

በሰባቱ ዩኒቨርስቲዎች የሚገነቡት ማዕከላት በየአካባቢው ያሉ ልዩ ልዩ ባህላዊና ተፈጥሮአዊ ሃብቶችን በቴክኖሎጂ በመደገፍ ወደ ሃብት መቀየር የሚቻልበትን ሁኔታም ይፈጥራሉ ተብሏል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም