ፍርድ ቤቱ የጥረት ኮርፖሬት ከፍተኛ አመራሮች የ14 ቀናት የጊዜ ቀጠሮን ለመመልከት ለመጪው ሰኞ ቀጠረ

65

ባህርዳር የካቲት 15/2011 የባህር ዳርና አካባቢ ከፍተኛ ፍርድ ቤት  በቀድሞ የጥረት ኮርፖሬት  ከፍተኛ አመራሮች የ14 ቀናት የጊዜ ቀጠሮ ጉዳይ ለመመልከት ለፊታችን ሰኞ ቀጠሮ ያዘ።

ፍርድ ቤት ዛሬ በዋለው ችሎት የኮርፖሬቱ የቀድሞ ከፍተኛ አመራሮች የነበሩት አቶ በረከት ስምኦንና አቶ ታደሰ ካሳ በተጠረጠሩበት የሙስና ወንጀል የቀረበውን ሰነድ በመመርመር በዐቃቤ ሕግ የተጠየቀውን የጊዜ ቀጠሮ ለመወሰን ለየካቲት 18/2011 ፍርድ ቤቱ ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡

ፍርድ ቤቱ ጉዳያቸው በታየው ሁለቱ ተጠርጣሪዎች የሰነድና የሰው ማስረጃ ማሰባሰቡን የአማራ ክልል ሥነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን ዐቃቤ ሕግ አቅርቧል፡፡

ነገር ግን አሁንም ወሳኝ የሆኑና በውጭ ሕክምና የሚከታተሉ ሁለት ምስክሮች ወደ አገር ውስጥ ባለመምጣታቸው የሰው ምስክሮችን አለማጠናቀቁን ገልጿል፡፡

እንዲሁም የዳሽን ቢራ ፋብሪካ የአክሲዮን ሽያጭ ሕግና ደንብን የተከተለ መሆን አለመሆኑን በዘርፉ ባለሙያዎች በመጣራት ላይ እንደሚገኝ ለፍርድ ቤቱ ቀርቧል፡፡

ሥራው የዕረፍት ቀናትን ጭምር በመጠቀም እየተሰራ ቢሆንም፤ ከውስብስብነቱ አንፃር ያልተጠናቀቁ ጉዳዮችን አጠናቅቆ ለማቅረብ የ14 ቀናት የጊዜ ቀጠሮ ጠይቋል፡፡

በጉዳዩ ላይ የመከራከሪያ ሃሳብ ያቀረቡት አቶ በረከት በበኩላቸው ዐቃቤ ሕግ በተጠየቀው ጊዜ ቀጠሮ ጉዳዩን አጠናቅቆ ማቅረብ እንደሚገባና አዳዲስ ሃሳቦች እየቀረቡ በእስር መቆየታቸው ተገቢ እንዳልሆነ ገልጸዋል፡፡

የፋብሪካው ኦዲት አልተጠናቀቀም የተባለው ፋብሪካው በየዓመቱ ኦዲት እየተደረገ መምጣቱን ከሰነዱ ማረጋገጥ ይቻላል ሲሉም ተናግረዋል፡፡

የፋብሪካው የአክሲዮን ሽያጭ ሰነድ በሰነዶች ማረጋገጫና ምዝገባ ጽህፈት ቤት በሕግ አግባብ የተያዘ በመሆኑ ጉዳዩን ማራዘም  ተገቢ አይደለም ብለዋል፡፡

በውጭ የሚገኙ ምስክሮች እነማን እንደሆኑ ለችሎቱ ግልፅ ይደረግ ሲሉም አቶ በረከት ጠይቀዋል፡፡

ኦዲት በማስደረግ፣ ምስክሮች በማሰባሰብ፣ ሰነድ በማስባሰብና የባንክ ጉዳዮችን ፍርድ ቤቱ በሰጠው የጊዜ ቀጠሮ ማጠናቀቅ ሲገባው አዳዲስ ጉዳችን እያመጡ ቀጠሮ መጠየቅ ተገቢ አይደለም ያሉት ደግሞ አቶ ታደሰ ካሳ ናቸው፡፡

''ምስክሮችን ከውጭ ይምጡ አይምጡ የእኛ ጉዳይ አይደለም'' ያሉት አቶ ታደሰ፣ ምስክሮች መምጣት ባይችሉ ፍርድ ቤት ልንመላለስ አይገባም ብለዋል፡፡

ስለሆነም ዐቃቤ ሕግ የሚፈልገውን ሰነድም ሆነ ማስረጃ በማሰባሰብ ፈጥኖ ክስ ሊመሰርትና ወደ ክርክሩ  መግባት እንጂ፤ ተጨማሪ  የጊዜ ቀጠሮ መጠየቅ አግባብ እንዳልሆነ ተናግረዋል፡፡

ዐቃቢ ሕግ በበኩሉ ፋብሪካው በየዓመቱ ኦዲት መደረግና ዐቃቤ ህግ እያደረገ የለው ኦዲት የማይገናኝ መሆኑን አስረድቷል፡፡

በጽህፈት ቤቱ የተያዘው ሰነድና የኮሚሽኑ መርማሪዎች እየፈለጉት ያለው ሰነድ ይለያያል ብሏል፡፡

በውጭ የሚገኙ ምስክሮችን በፍጥነት እንዲመጡ ለማድረግ እየተሰራ ነው ያለው ዐቃቤ ሕግ፣ የምስክሮችን ማንነት ለመግለጽ እንደማይገደድ ገልጿል።ሆኖም ችሎቱ አስፈላጊ ነው ብሎ ካመነ በቀጣይ ሊገልጽ እንደሚችል አስታውቋል፡፡

በክሱ ሂደት በምርመራ ወቅት የሚገኙ አዳዲስ ጉዳዮች እንደሚካተቱ የገለጸው ዐቃቤ ሕግ፣ ያልጠናቀቁና መጠናቀቅ የሚገባቸው አስፈላጊ ጉዳዮች በመኖራቸው ተጨማሪ የ14 ቀናት ቀጠሮ ጠይቋል፡፡

ዐቃቤ ሕግ ያቀረበውን ሰነድ በመመርመር የ14 ቀን የጊዜ ቀጠሮ ያስፈልጋል ወይም አያስፈልግም የሚለውን ለመወሰን የቀረበውን ሰነድ ለመመርመርና ለመወሰን ለሰኞ የካቲት 18/2011 ተለዋጭ ቀጠሮ በመስጠት ችሎቱን አጠናቋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም