የንግዱን ማህበረሰብ የተጨማሪ እሴት ታክስ አከፋፈል ስርአት ማሻሻል እንደሚገባ ተጠቆመ

80

ደብረ ማርቆስ የካቲት 15/2011 የንግዱን ማህበረሰብ የተጨማሪ እሴት ታክስ አከፋፈል ስርአት በማሻሻል የተጀመረውን ሀገራዊ ልማትና የለውጥ እንቅስቃሴ ማስቀጠል እንደሚገባ ተገለጸ።

በምስራቅ ጎጃም ዞን እስከ ሰኔ 30 ቀን 2011 የሚቆይ የተጨማሪ እሴት ታክስ የንቅናቄ መድርክ በደብረማርቆስ ከተማ እየተካሄደ ነው።

የአማራ ክልል ገቢዎች ቢሮ ኃላፊ ሲስተር ብዙአየሁ ቢያዝን በእዚህ ወቅት እንዳሉት ለሀገር እድገት  ግብር  ትልቁን ድርሻ ይይዛል።

በመሆኑም በሀገሪቱ የንግዱን ማህበረሰብ የተጨማሪ እሴት ታክስ አከፋፈል ስርአትን በማሻሸል የተጀመረውን ልማትና ሀገራዊ ለውጥ ማስቀጠል አንደሚገባ ተናግረዋል።

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በግብር አካፋፈል ላይ የሚስተዋሉ ችግሮች እየተሻሻሉ ቢሆንም ተጨማሪ እሴት ታክስን ለመንግስት የማስገባት ግዴታ በአግባቡ እየተተገበረ አለመሆኑን አስረድተዋል።

"እየተካሄደ ያለው የንቅናቄ መድረክ ዓላማም የግብር ከፋዮን ማህበረሰብ ግንዛቤን በማሳደግ ግብርን በተነሳሰሽነት የመክፈል ባህሉን ማሳደግና በዘርፉ የሚስተዋሉ ችግሮችን ለመፍታት ምቹ ሁኔታ ለመፍጠር ነው" ብለዋል።

የዞኑ ዋና አስተዳደሪ አቶ አብርሃም አለኽን በበኩላቸው እንደተናገሩት ህዝቡ በሚያነሳቸው የመሰረተ ልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች ልክ መልስ እንዲያገኝ በተነሳሽነት ግብር የመክፈል ልምዱን ሊያዳብር ይገባል።  

"ህብረተሰቡ ግብር መክፈል ጠቀሜታው ለራስ መሆኑን ማወቅ አለበት" ያሉት አቶ አብርሀም፣ የሚከናወኑ የልማት ሥራዎች ተጠናክረው እንዲቀጥሉና የተጀመረውን ሀገራዊ ለውጥ ለማስቀጠል ግብርን በአግባቡ መሰብሰብ ወሳኝ መሆኑን አመልክተዋል። 

በዞኑ ካለፈው ዓመት አንስቶ የሚሰበሰበው ግብር ከዕቅድ ጋር የተጣጣመ ቢሆንም በእሴት ታክስ አከፋፈል ላይ ግን በተለያዩ ምክንያቶች የጎላ ክፍተት መኖሩን ገልጸዋል።

"ሁሉም የማህበረሰብ ክፍል ታክስ ማጭበርበር ራሱንና ሀገርን እንደመስረቅ አድርጎ ሊያስበው ይገባል" ያሉት አቶ አብርሃም እስከ ሰኔ ወር መጨረሻ የሚካሄደው የንቅናቄ መድረክ ግንዛቤ በመፍጠር በኩል አስተዋጽኦ እንደሚኖረው ተናግረዋል።

የምስራቅ ጎጃም ዞኑ ገቢዎች ቅርንጫፍ ጽፈት ቤት ኃላፊ ወይዘሮ ገነት በቀለ በበኩላቸው ገቢን በማሳደግ ልማትን ለማፋጠን ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

በተወሰኑ ነጋዴዎች ላይ የሚስተዋለው ደረሰኝ አለመስጠት፣ የተሳሰተ ደረሰኝ መቁረጥ እና ገቢን መቀነስ የተጨማሪ እሴት ታክስ ገቢ በተፈላገው ልክ እንዳያድግ እንቅፋት መፍጠሩን አስረድተዋል።

በዞኑ ከ1 ሺህ 470 በላይ የተጨማሪ እሴት ታክስ ተመዝጋቢ ነጋዴዎች በበጀት ዓመቱ እስከ ጥር 30 ቀን 2011 ባለው ጊዜ ከ55 ሚሊዮን ብር በላይ ገቢ ለመሰብሰብ ቢታቀድም መሰብሰብ የተቻለው 20 ሚሊዮን ብር ብቻ መሆኑን ተናግረዋል።

ለእሴት ታክስ ገቢ መቀነስ የንግዱ ማህበረሰብ ችግር ብቻ ሳይሆን የአመራሩ በጥልቀትና በተከታታይ ግንዘቤ አለመፍጠር እንዲሁም ተገልጋዩ ማህበረሰብ የተጠቀመበትን ደረሰኝ የመቀበል ልምድ አናሳ መሆን ተጠቃሽ ምክንያት መሆናቸውን አስረድተዋል።

በቀጣይ አመራሩ የችግሩን ስፋት በመረዳት ተገቢውን ድጋፍና እገዛ ሊያደርግ ይገባል፡፡

እንደኃላፊዋ ገለጻ በበጀት ዓመቱ በመደበኛና በከተማ አገልግሎት ገቢ ከ866 ሚሊዮን ብር በላይ ለመሰብሰብ የታቀደ ሲሆን እስካሁንም ከሁለቱም የገቢ አርስቶች ከ458 ነጥብ 4 ሚሊዮን ብር በላይ ለመሰብሰብ ተችሏል።

እስከ ሰኔ 30 ቀን 2011 እየተካሄ ባለው የንቅናቄ መድረክ ከሃይማኖት ተቋማት፣ ከንግዱ ማህበረሰብ፣ ከተማሪ፣ ከመንግስት ሰራተኞች፣ ከሴቶችና ከወጣቶች የተወከሉ የህብረተሰብ ክፍሎች የግብርና ታክስ አምባሳደር ሆነው ቅስቀሳ በማድረግ ላይ ናቸው።

በምስራቅ ጎጃም ዞን ከ35 ሺህ በላይ ግብር ከፋይ ነጋዴዎች እንዳሉ ለማወቅ ተችሏል።  

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም