በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የሴቶችን ተሳትፎ ለማሳደግ አስፈላጊው ትብብር እንዲደረግ ተጠየቀ

761

አዲስ አበባ  የካቲት 14/2011 በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የሴቶችን ተሳትፎ ለማሳደግ አስፈላጊው ትብብር እንዲደረግ ፕሬዝዳንት ሣህለወርቅ ዘውዴ ጥሪ አቀረቡ።

በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የሥርዓተ ጾታ እኩልነትን ለማስፈን በተመለከተ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የአፍሪካ ኢኮኖሚ ኮሚሽን መሰብሰቢያ አዳራሽ ዛሬ ውይይት ተካሂዷል። 

ፕሬዝዳንት ሣህለወርቅ ዘውዴ በዚሁ ጊዜ እንዳሉት በዝቅተኛ ትምህርት ደረጃዎች ሴቶች ያላቸው ተሳትፎ ጥሩ ቢሆንም ከፍ እያለ ሲመጣ ግን ይህ ተሳትፏቸው ዝቅተኛ ነው።

በተለይም የሦስተኛ ዲግሪ ምሩቅ የሆኑና ከዩኒቨርሲቲ ተመርቀው በከፍተኛ የኃላፊነት ሥራ ላይ የሚመደቡ ሴቶች ቁጥር ከሚጠበቀው በታች መሆኑን አስረድተዋል።

”ይህ ደግሞ በአንደኛና በሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች የሚማሩ ሴቶች አርአያ የሚያደርጓቸው ሴቶች ስለሚያጡ ችግሩን ተመላላሽ ሊያደርገው ይችላል” ብለዋል።

ለዚህም የዩኒቨርሲቲ አመራርና ማኅበረሰቡ እንዲሁም ኀብረተሰቡ ርብርብ በማድረግ ሴቶች በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ያላቸውን ተሳትፎ ማሳደግ እንደሚገባቸው አሳስበዋል።

በአሁኑ ወቅት ሴቶች ወደ ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊነት ቦታ መምጣታቸው በሴቶች አመለካከት ላይ ዓይነተኛ ሚና እንደሚኖረውም አውስተዋል። 

የሳይንስና የከፍተኛ ትምህርት ሚኒስትር ፕሮፌሰር ሂሩት ወልደማርያም በበኩላቸው የሴቶች ተሳትፎ በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ከሚጠበቀው በታች መሆኑን ተናግረዋል። 

እንዲሁም በዩኒቨርሲቲዎች የኃላፊነት ቦታ ላይ ያላቸው ተሳትፎም ዝቅተኛ መሆኑን ጠቁመዋል።

አሁንም ባህላዊና ልማዳዊ የወንድና የሴት የሥራ ድልድል ያለ ቢሆንም ሴቶች ግን በማኀበረሰቡ ውስጥ የተደራራቢ ሚና ባለቤት እንደሆኑ አብራርተዋል።  

ይህን ችግር ለማስቀረት ከፍተኛ ትኩረት ሊደረግበት እንደሚገባ የጠቆሙት ፕሮፌሰሯ፤ በተለይም አርአያ የሚሆኑ ሴቶችን ወደፊት ለማምጣት ርብርብ ማድረግ ያስፈልጋል ብለዋል። 

በዩኒቨርሲቲ አመራር የሴቶችን ተሳትፎ ለማሳደግ ቢያንስ ሁለት የሴት አመራር በከፍተኛ የሥራ አስፈጻሚ ቦታዎች ላይ ምደባ እንዲያገኙ የሚያደርግ አሰራር መዘርጋቱንም ጠቁመዋል።

የሴቶች ቁጥር በቅድመ ምረቃ ከአጠቃላይ ተመራቂዎች 34 በመቶ፣ በሁለተኛ ዲግሪ ደግሞ 17 በመቶ እንዲሁም በሦስተኛ ዲግሪ ስምንት በመቶ መሆኑን ከሚኒስቴሩ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

በኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት 45 የመንግሥት ዩኒቨርስቲዎችና 170 የግል የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት አሉ።