ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ከኡራጋይ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጋር በሁለትዮሽ ግንኙነት ዙሪያ ተወያዩ

61

አዲስ አበባ  የካቲት 14/2011 ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ የኡራጋይ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሮዶልፎ ኒን ኖቫዎን ዛሬ በብሔራዊ ቤተ መንግስት ተቀብለው አነጋግረዋል።

በኢትዮጵያ የስራ ጉብኝት በማድረግ ላይ የሚገኙት የኡራጋይ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ከፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ጋር በነበራቸው ቆይታ በኢትዮጵያና ኡራጋይ መካከል በትብብር መስራት በሚቻልባቸው ጉዳዮች ላይ ተወያይተዋል።

ሚኒስትሩ በቃል አቀባያቸው በኩል ለኢዜአ እንደገለጹት፤ ኢትዮጵያና ኡራጓይ በዕውቀት ሽግግርና በግብርና ልማት በትብብር መስራት በሚችሉባቸው ጉዳዮች ላይ ውይይት ተደርጓል፤ በጋራ ለመስራትም ስምምነት ላይ ተደርሷል። 

በአፍሪካ አራት ኤምባሲዎች ያሏት ኡራጋይ አንዱን በኢትዮጵያ መክፈቷን ያስታወሱት ቃል አቀባዩ ኡራጋይ ኤምባሲዋን በአዲስ አበባ መክፈቷ አገሪቱ ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን ግንኙነት የማጠናከር ፍላጎት እንዳላት የሚያሳይ እንደሆነ ገልጸዋል።

ውይይቱን የተከታተሉት የፕሬዚዳንት ጽህፈት ቤት የፕሮቶኮልና የኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክተር አቶ አሸብር ጌትነት እንደገለጹት፤ ሁለቱ አገሮች በተለያዩ ዘርፎች በትብብር የሚያከናውኗቸውን ስራዎች ለማጠናክር የሚያስችል ውይይት አድርገዋል።

ባለፈው ዓመት ሰኔ ወር ላይ የኡራጋይ አፍሪካ የንግድ ምክር ቤት ባዘጋጀው የንግድ ማህበረሰብ ስብሰባ ላይ የኢትዮጵያ የንግድ ማህበረሰብ ልዑካን ወደ ኡራጋይ አቅንቶ በአገሪቱ ያለውን ምቹ ሁኔታ ተመልክቶ መምጣቱ ይታወሳል።

በስብሰባው ላይ የአግሮ ኢንዱስትሪና ምግብ፣ የኤሌክትሪክ እቃዎች አቅራቢ፣ የጉዞና ቱሪዝም፣ የሪል ስቴትና ኮንስትራክሽን እንዲሁም የኬሚካል አምራች ኩባንያዎች ተሳትፈዋል።

ኢትዮጵያ በላቲን አሜሪካ ያሏት ኤምባሲዎች ውስን በመሆናቸው በብራዚል የሚገኘው ኤምባሲ የኡራጋይን የዲፕሎማሲ ግንኙነት ተልዕኮ እንዲሰራ ሃላፊነት ተሰጥቶታል።

ኡራጋይ እንደ አውሮፓዊያኑ አቆጣጠር 2016 ጀምራ በአዲስ አበባ ኤምባሲዋን ከፍታ እየሰራች ትገኛለች።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም