ከተሞችን የሰላም፣ የልማትና የለውጥ መናኸሪያ ማድረግ ይገባል - የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ሚኒስትሩ

102

አዲስ አበባ የካቲት 14/2011 የኢትዮጵያ ከተሞችን የሰላም፣ የልማት፣ የለውጥ መተግበሪያና የመልካም አስተዳደር መናኸሪያ ለማድረግ የሚያስችሉ ተግባራት መከናወን እንዳለባቸው የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ሚኒስትሩ አሳሰቡ።

"መደመር ለኢትዮጵያ ከተሞች ብልጽግና" በሚል በሱማሌ ክልል ጅግጅጋ ከተማ ላለፈው አንድ ሳምንት የተካሄደው 8ኛው የከተሞች ፎረም ዛሬ ተጠናቋል።

በዚሁ ጊዜ የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ሚኒስትሩ  አቶ ጃንጥራር አባይ እንደገለጹት በአገሪቱ የተጀመረው ለውጥ እንዲቀጥል ከተሞች ነዋሪዎቻቸውን የሚያረኩ አገልግሎቶችን ለማጠናከር ተግቶ መሥራት ይገባል። 

ለዚህም በየጊዜው ከሚዘጋጁ የከተሞች ፎረም ልምድና ተሞክሮ በመውሰድ ከተሞች የሰላም፣ የልማት፣ የለውጥ መተግበሪያና የመልካም አስተዳደር መናኸሪያ ማድረግ ይጠበቃል ብለዋል።

ከተሞችን የሚያሰባስቡ ይህን የመሰሉ ፎረሞች ለከተማ እድገትና ልማት የሚፈይዱ ልምዶችን ከመካፈል ባሻገር አብሮነትንና አንድነትን ለማጎልበትም ዓይነተኛ መሳሪያ መሆናቸውን ጠቅሰዋል።

ከተሞች የሁሉም ኢትዮጵያያዊያን መኖሪያ መሆናቸውን በመገንዘብ መላው ህዝብ በደምና በጎሳ ሳይለያይ በጋራ የሚኖሩባቸው ስፍራዎች እንዲሆኑ ማድረግ ተገቢ ነው ሲሉም ሚኒስትሩ አሳስበዋል።

"ዛሬ የተጠናቀቀው 8ኛው የከተሞች ፎረምም ይህንን እውን ለማድረግ ቃል ኪዳን የሚገባበት መድረክ ሊሆን ይገባል" ሲሉ ተናግረዋል።

የሱማሌ ክልል ምክትል ርእሰ መስተዳደር አቶ ሙስጠፋ ሙሃመድ ዑመር በበኩላቸው  ተሳታፊ ከተሞችን ጨምሮ ፎረሙ በስኬት እንዲጠናቀቅ የበኩላቸውን ሚና ለተጫወቱ አካላት ምስጋና አቅርበዋል።

ፎረሙ የአገሪቷ ከተሞች ያላቸውን ልምድና ተሞክሮ የተለዋወጡበት መሆኑን ጠቅሰው በተለይም የጅግጅጋ ከተማን ጨምሮ ሌሎች የክልሉ ከተሞችም ጥሩ ልምድና ተሞክሮ አግኝተዋል ብለዋል።

በፎረሙ የጎረቤት አገራቱ ጅቡቲ፣ ሀርጌሳና በርበራ እንደዚሁም ከሁሉም የኢትዮጵያ ክፍሎች የመጡ 170 ከተሞች ልኡካን ቡድን አባላት ተሳትፈዋል።

በኢትዮጵያ ከአራት ዓመታት በፊት 972 የነበረው የከተሞች ብዛት በአሁኑ ወቅት ከእጥፍ በላይ አድጓል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም