ኢቦላን ለመከላከል የአፍሪካ አገራት ጠንካራ አመራር ሊያሳዩ ይገባል – የዓለም ጤና ድርጅት

783

የካቲት አዲስ አበባ 14/6/2011 በአህጉር አቀፍ ደረጃ የኢቦላ ቫይረስን ለመከላከል የአፍሪካ አገራት ጠንካራ የአመራር ቁርጠኝነት ሊያሳዩ ይገባል ሲል የዓለም የጤና ድርጅት ገለጸ።

የአፍሪካ ህብረት፣ የአፍሪካ የበሽታዎች መከላከያና መቆጣጠሪያ ማዕከል እና የዓለም ጤና ድርጅት በአህጉር ደረጃ ኢቦላን መከላከል እየተሰሩ ባሉ ስራዎችና በዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ሰሜን ኪቩ ግዛት ያለውን የኢቦላ ስጋት አስመልክቶ በጋራ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል።

የዓለም የጤና ድርጅት የአፍሪካ ቢሮ የአደጋ ጊዜ ምላሽ ዳይሬክተር ዶክተር ኢብራሂማ ሴስ ፋል እንዳሉት ድርጅቱ በአፍሪካ ኢቦላን ለመግታት ከአፍሪካ ህብረት ጋር በትብብር እየሰራ ነው።

የህብረቱ አባል አገራት የኢቦላ ቫይረስን የመከላከልና የመቆጣጠር ተቋማዊ ብቃት ላይ ያለባቸውን ክፍተት ለመሙላት የአቅም ግንባታ ስልጠናና የቴክኒክ ድጋፍ እያደረገ መሆኑንም ተናግረዋል።

በተጨማሪም ቫይረሱ በሚከሰትባቸው አካባቢዎች ከአፍሪካ ህብረት የአፍሪካ የበሽታዎች መከላከያና መቆጣጠሪያ ማዕከልና ከሌሎች አጋር አካላት ጋር በመሆን ክትባትን ጨምሮ የህክምና አገልግሎት እየሰጠ መሆኑን ገልጿል።

በአህገሪቱ ኢቦላን ለመከላከል አጋር አካላት ከሚያደርጉት ድጋፍ በተጨማሪ የአፍሪካ ህብረት አባል አገራት በሽታውን ለመግታት ጠንካራ አመራር ሊያሳዩ እንደሚገባ ነው የገለጹት።

በአጠቃላይ ለኢቦላ ብቻ ሳይሆን ሌሎች በሽታዎችን ለመከላከል የአፍሪካ አገራት የሚመድቡትን በጀት ማሳደግና የአደጋ ጊዜ ምላሽ አቅማቸውንና የጤና ተቋማትን ብቃት ማሳደግ ላይ በትኩረት ሊሰሩ ይገባል ብለዋል።

እንደ አውሮጳውያን አቆጣጠር ከ2014 እስከ 2016 በሴራሊዮን፣ ጊኒ፣ ላይቤሪያ እንዲሁም በናይጄሪያ፣ ሴኔጋልና ማሊ የተወሰኑ አካባቢዎች ተከስቶ የነበረውን የኢቦላ ወረርሽኝ በጋራ ርብርብ መቆጣጠር መቻሉን አውስተዋል።

በዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ሰሜን ኪቩ ግዛት ቫይረሱ እንደ አውሮጳውያን አቆጣጠር በነሐሴ 2018 በድጋሚ ከተከሰተ በኋላ እስከ ትናንት ድረስ ባለው መረጃ እስካሁን 848 ሰዎች በቫይረሱ መያዛቸውንና ከነዚህም 529ኙ መሞታቸውን ጠቅሰዋል።

ከነዚህ መካከል የተወሰኑት አሟሟት ከኢቦላ ቫይረስ ጋር የተያያዘ መሆን አለመሆኑ እየተጣራ መሆኑንና ድርጅቱን ጨምሮ ሌሎች አጋር አካላትና የአገሪቱ መንግስት በሽታውን ለመከላከል እየሰሩ መሆኑን ገልጸዋል።

በተጨማሪም ቫይረሱ ከዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ አልፎ ወደ ጎረቤት አገራት እንዳይዛመት የህክምና ምርምራ የማድረግና የመቆጣጠር ተግባር እየተከናወነ ነው ብለዋል።

የአፍሪካ የበሽታዎች መከላከያና መቆጣጠሪያ ማዕከል ዳይሬክተር ዶክተር ጆን ንኬንካሶንግ በበኩላቸው ከየትኛውም ጊዜ በበለጠ ኢቦላን ለመግታት የሚያስችል አጋጣሚ መኖሩን ተናግረዋል።

በአሁኑ ወቅት የኢቦላ ቫይረስን ለመከላከል የሚያስችሉ ክትባቶችና ህክምናዎች በስፋት መኖራቸውን፤ በተለይም ክትባቶቹ ተጨባጭ ውጤት እያመጡ መሆኑን አስታውቀዋል።

በሰሜን ኪቩ ግዛት ያለው የጸጥታ ሁኔታ ስራዎች በሚፈለገው መልኩ እንዳይሄዱ ማድረጉንና በግዛቱ ያሉ ሃይሎችና መንግስት የህክምና እርዳታው ያለ ምንም መስተጓጎል እንዲካሄድ አስፈላጊውን ትብብር ማድረግ እንዳለባቸው አሳስበዋል።

የኢቦላ ቫይረስ ለመጀመሪያ ጊዜ በአፍሪካ የተከሰተው እንደ አውሮጳውያን አቆጣጠር በ1976 በቀድሞዋ ሰሜን ዛየር በአሁኗ ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ነበር።