የስምንት ከተሞች የኔትወርክ ማሻሻያ ስራን 93 በመቶ አጠናቅቄያለሁ … የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት

47

አዲስ አበባ የካቲት 14/2011 በስምንት ከተሞች እያከናወነ ያለው የኔትወርክ ማሻሻያ ስራ ሙሉ በሙሉ ተጠናቆ አገልግሎት መስጠት ሊጀምር መሆኑን የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት አስታወቀ።

የኔትወርክ ማሻሻያ ስራው በ67 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር ብድርና የኢትዮጵያ መንግስት በመደበው 147 ሚሊዮን ብር የተገነባ ነው።

የአገልግሎቱ ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ሽፈራው ተሊላ የተቋሙን የስድስት ወር አፈጻጻም አስመልክተው ዛሬ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ የኔትወርክ ማሻሻያ ስራው በተያዘው በጀት ዓመት ተጠናቆ አገልግሎት መስጠት ይጀምራል።

ግንባታው በአዲስ አበባ፣ ባህር ዳር፣ መቀሌ፣ ደሴ፣ ድሬደዋ፣ አዳማ ፣ሀዋሳና ጅማ ሲሆን አጠቃላይ የኔትወርኩ የመልሶ ግንባታና የማሻሻያ ስራ 93 በመቶ መድረሱን ተናግረዋል።

የኔትወርክ ማሻሻያው መጠናቀቅ ጥራት ያለው አገልግሎትን ለመስጠት፣  አገልግሎቶቹ ከአደጋ  ለመታደግ ያስችላልም ብለዋል።

የኔትወርክ ማሻሻያ የተደረገው ፈትሃዊ የኤሌከትሪክ አገልግሎትን ለማዳረስ ታስቦ ሲሆን ይህም ሰፊ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ በሚካሄድባቸው በተመረጡ የአገሪቷ ከተሞች ነው።

የኔትወርክ ማሻሻያው በቀጣይ በሻሻመኔ፣ ጎንደር፣ ወላይታ ሶዶ፣ ሀረር፣ ደብረብርሃንና ደብረማርቆስም ለቀጠል የቅድመ ዝግጅት ስራው ተጠናቆ በሶስት ከተሞች ተግባራዊ በመደረግ ላይ ነውም ብለዋል።

አንዳንድ ጥገናና ማሻሻያ የተደረገላቸው የኔትወርክ አገልግሎቶች ወደ ስራ የገቡ ሲሆን መሉ በመሉ ወደ ስራ ሲገቡ በአካባቢዎቹ የተሻለ የኤሌክትሪክ አገልግሎት እንደሚኖር ተናግረዋል።

ባለፉት ስድስት ወራትም ከ90 ሺህ በላይ አዳዲስ ደንበኞች  የሃይል አቅርቦት እንዳገኙ አቶ ሽፈራው ተናግረዋል።

አገልግሎቱ በበጀት ዓመቱ ስድስት ወር ጊዜ ተቋሙ ከተለያየ ዘርፎች ከ3 ቢሊዮን ብር በላይ ገቢ ማግኘቱን ጠቁመው ከ1999 ዓ.ም ጀምሮ ከደንበኞች ያልተሰበሰቡ 665 ሚሊዮን ብር መሰብሰቡንም ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም