በኢሉአባቦር ዞን በ12 ሚሊዮን ብር እየተገነቡ ካሉ የመስኖ ፕሮጀክቶች ሁሉቱ ተጠናቀው ለአገልግሎት በቁ

373

መቱ የካቲት 14/2011 በኢሉአባቦር ዞን በ12 ሚሊዮን ብር ወጪ ግንባታቸው በመካሄድ ላይ ከነበሩ ስድስት ዘመናዊ የመስኖ ፕሮጀክቶች መካከል ሁለቱ ተጠናቀው ለአገልግሎት በቁ፡፡

የዞኑ ቡና፣ እርሻና ተፈጥሮ ሀብት ልማት ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ጌታሁን ለገሰ ለኢዜአ እንዳሉት የመስኖ ፕሮጀክቶቹ በቅርቡ ተጠናቀው ለአገልግሎት የበቁት በቡሬና መቱ ወረዳዎች ነው።

ፕሮጀክቶቹ በአንድ ጊዜ 90 ሄክታር መሬት የማልማት አቅም ያላቸው ሲሆን በልማቱም 360 በምግብ ዋስትና የታቀፉ አርሶ አደሮች በማሳተፍ ተጠቃሚ እንደሚያደርጉ አመልክተዋል። 

ካለፉት ሁለት ዓመታት ወዲህ ግንባታቸው በመካሄድ ላይ የነበሩት ሌሎች አራት የመስኖ ፕሮጀክቶች በአሁኑ ወቅት ከ80 በመቶ በላይ መገንባታቸውን የገለጹት ኃላፊው በዚህ ዓመት ሙሉ በሙሉ በማጠናቀቅ ስራ ለማስጀመር ጥረት እየተደረገ ይገኛል።

የተጠናቀቁትና ግንባታቸው በሂደት ላይ የሚገኙ ፕሮጀክቶች ሙሉ ለሙሉ ስራ ሲጀምሩ ከአንድ ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በማልማት 3 ሺህ አርሶ አደሮችን ተጠቃሚ ያደርጋሉ ተብሎ ይጠበቃል።

በቡሬ ወረዳ ቶሊ ጬካ ቀበሌአርሶ አደር ጌታቸው ቀኖ በሰጡት አስተያየት ከዚህ ቀደም ከውሃ እጥረት የተነሳ በባህላዊ መስኖ ልማት ከሁለት ጥማድ ያልበለጠ ማሳ ብቻ ሲያለሙ መቆየታቸውን አስታውሰዋል፡፡

ለአገልግሎት በበቃው ዘመናዊ የመስኖ ፕሮጀክት በመጠቀም በሁለት ሄክታር ማሳቸው ላይ ቀይስር፣ ካሮትና ሽንኩርት ዘርተው እየተንከባከቡ መሆናቸውን ተናግረዋል።

በዘንድሮ ዓመት በማህበር ተደራጅተው ለመጀመርያ ጊዜ መስኖ ልማት ሥራ ውስጥ መግባታቸው የገለጹት ደግሞ ሌላኛው የቀበሌው አርሶ አደር አምቢሳ ይገዙናቸው፡፡

የዘመናዊ መስኖ ተጠቃሚ በመሆናቸው በአጭር ጊዜ ውስጥ ሕይወታቸውን ለመለወጥ መነሳሳታቸውን ተናግረዋል።

በኢሉአባቦር ዞን በዚህ ዓመት ከ41 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በሁለት ዙር በመስኖ ለማልማት ታቅዶ እየተሰራ ሲሆን እስካሁንም ከ14 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት ለምቷል።

በሁለት ዙር ይለማል ተብሎ ከሚጠበቀው አጠቃላይ መሬት ከአራት ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት ይገኛል ተብሎ ይጠበቃል፡፡