በዋግ ኽምራ ግብርን የሚሰውሩ ነጋዴዎች መበራከት በግብር አሰባሰብ ላይ ተጽዕኖ እያሳደረ ነው

65

ሰቆጣ  የካቲት 13/2011 በአማራ ክልል ዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አስተዳደር ግብርን የሚሰውሩ ነጋዴዎች መበራከት በግብር አሰባሰብ ላይ ተፅዕኖ መፍጠሩን የአስተዳደሩ ገቢዎች ቅርንጫፍ ፅህፈት ቤት አስታወቀ፡፡

"ግዴታዬን እወጣለሁ መብቴን እጠይቃለሁ" በሚል መሪ ቃል በብሔረሰቡ አስተዳደር የግብርና የታክስ ፎረም ተካሂዷል፡፡

የጽህፈት ቤቱ ሥራ አስኪያጅ አቶ ኃይሌ አምሳሉ ለኢዜአ እንደገለፁት የንቅናቄ ፎረሙ የተዘጋጀው የግብር ከፋዩን ማህበረሰብ ግንዛቤ በማሳደግ ግዴታውን እንዲወጣ ለማድረግ ነው፡፡

በዘርፉ የሚስተዋሉ ችግሮችን ለመቅረፍ ጽህፈት ቤቱ ተቋማዊ አሰራርና አደራጀጅትን በማሻሻል በማህበረሱ የሚነሱ ቅሬታዎችን ለመፍታት  ሰፊ ሥራ እየተሰራ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡

አቶ ኃይሌ እንዳሉት የሚጠበቅባቸውን ግብር በወቅቱና በአግባቡ የሚከፍሉ ግብር ከፋዮች የመኖራቸውን ያህል ግብር ላለመክፈል ዜሮ ሪፖርት የሚያቀርቡ ነጋዴዎች እየተበራከቱ መምጣት የሚፈለገውን ገቢ ለመሰብሰብ ተጽዕኖ ፈጥሯል።

በእዚህም በበጀት ዓመቱ ለመሰብሰብ ከታቀደው 148 ሚሊዮን ብር እስካሁን ግማሽ ያህሉን እንኳ ለመሰብሰብ እንዳልተቻለ አመላክተዋል፡፡

ግብርን በሚያጭበረብሩ ነጋዴዎች ላይ ህጋዊ ርምጃ ለመውሰድ የምርመራ ሂደት ላይ መሆናቸውን የገለጹት ሥራ አስኪያጁ ህበረተሰቡ ህጋዊ አሰራርን ለማስፈን በሚደረገው ጥረት ተገቢውን ድጋፍ እንዲያደርግ ጥሪ አቅርበዋል።

የብሔረሰቡ አስተዳደር ምክትል አስተዳዳሪና የንግድ መምሪያ ኃላፊ አቶ አበበ ተቀባ በበኩላቸው በዞኑ በርካታ የዛፍ ጥላና የዳስ ትምህርት ቤቶች እንዲሁም ከደረጃ በታች ያሉ የጤና ተቋማት ይገኛሉ፡፡

" ህብረተሰቡ ደረጃውን በጠበቀ መልኩ በአቅራቢያው የጤና እና የትምህርት ተቋማትን አገልግሎት እንዲያገኝ ለማድረግ የሚጠበቅበትን ግብር በአግባቡ መወጣት ይኖርበታል " ብለዋል፡፡

በንግዱ ማህበረሰብ እምነትን በሚያጎለብት መልኩ ተቋማዊ አሰራርን በመዘርጋት ፍትሃዊ የግብር ስርአትን ማስፈን እንደሚገባ ጠቁመዋል፡፡

ህብረተሰቡ ግብር የህልውና ጉዳይ አድርጎ በመቁጠር ግዥ በፈፀመበት ልክ ደረሰኝ የመቀበል ልምዱን ማሳደግ አለበት ያሉት ምክትል አስተዳዳሪው ህግን የሚጥሱ ነጋዴዎች ሲገጥሙትም ጥቆማ እንዲሰጥ አመልክተዋል፡፡

በሰቆጣ ከተማ በምግብና መጠጥ ዘርፍ የተሰማሩትና በዕለቱ የታክስ አምባሳደር በመሆን የተሾሙት ወይዘሮ ዘበናይ ላቀው በበኩላቸው በተሰማሩበት የንግድ ዘርፍ በታማኝነት መስራት በመቻላቸው ለታክስ አምባሳደርነት በመሾማቸው ኩራት እንደተሰማቸው ተናግረዋል፡፡

"የከተማዋ የመልማት ፍላጎት በግብር ከፋዩ ህብረተሰብ ጭምር ይወሰናል" ያሉት ወይዘሮ ዘበናይ በቀጣይም በሰሩት ልክ የተጣለባቸውን ግብር ለመክፈል በታማኝነት እንደሚሰሩ አረጋግጠዋል፡፡

የተጣለብኝን ግብር በወቅቱ በመክፈል የዜግነት ግዴታየን እየተወጣሁ ነዉ፣  ሌሎች በንግድ የተሰማሩ ማህበረሰቦችም በታማኝነት ሊሰሩ ይገባል" ያሉት ደግሞ በሸቀጣሸቀጥና በእንስሳት ንግድ ሥራ የተሰማሩት አቶ ክብረት አበራ ናቸው።

"በቀጣይም ግብራቸውን በአግባቡ ከምክፈል ባለፈ ህግን በሚጥሱ ነጋዴዎችን በመጠቆም ኃላፊነቴን እወጣለሁ‘’ ብለዋል፡፡

በንቅናቄ ፎረሙ ነጋዴዎች፣ መንግስት ሰራተኞች፣ ተማሪዎች እና በዞኑ የሚገኙ የገቢ ተቋም ሰራተኞች የተሳተፉ ሲሆን በስፖርታዊ በልዩ ልዩ የኪነጥበብ ስራዎች ፎረሙ መካሄዱም ታውቋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም