ሚኒስቴሩ የጤና ተቋማት የግንባታ አፈጻጻም ብቃትን ለማሻሻል እየተሰራ መሆኑን ገለጸ

146

ጅማ የካቲት 13/2011 የጤና ተቋማት የግንባታ አፈጻጻም ብቃትን በማሻሻል የአገልገሎት አሰጣጡን ለማሳደግ እየተሰራ መሆኑን የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር አስታወቀ ፡፡

ሚኒስቴሩ በጤና ተቋማት የግንባታ አፈጻፀም ላይ ያተኮረ ውይይት በጅማ ከተማ ባካሄደበት ወቅት የመብራትና የውሃ ችግር ለአገልገሎት አሰጣጡ ፈተና እየሆነ መምጣቱ ተመልክቷል።

በጤና ጥበቃ ሚኒስቴር የጤና መሰረተ ልማት ዳይሬክተር  አቶ ታደሰ ይልማ እንዳሉት  ውይይቱ የተካሄደው በጤና ተቋማት ግንባታ ውስጥ የሚታዩ ችግሮችን በመለየት የመፍትሔ  አቅጣጫ ለማስቀመጥ  ነው ፡፡

በአገር አቀፍ ደረጃ የጤና ኬላና የጤና ጣቢያ ግንባታ በተሻለ መልኩ ተደራሽነት ማድረግ ቢቻልም እንደ መብራትና ውሃ የመሳሰሉ የመሰረተ ልማትን የማሟላት  ችግር መኖሩን ጠቁመዋል፡፡

በኢትዮጵያ ካሉት 4 ሺህ 956 ጤና ጣቢያዎች መካከል 1 ሺህ የሚሆኑት የውሃና የኤሌክትሪክ ኃይል አገልግሎት እንደማያገኙ ዳይሬክተሩ ጠቅሰዋል፡፡

ከዚህ ቀጥሎ ከፍተኛ ችግር የሚስተዋለው በመጀመሪያ ደረጃ የሆስፒታሎች ግንባታ መጓተት፣የጥራት ማነስና በተገባው ውል መሰረት  ያለማጠናቀቅ ነው ፡፡

ተያይዞም በ67 የስራ ተቋራጮች ላይ ውል የማቋረጥ እርምጃ መወሰዱን አመልክተው በአማራና ኦሮሚያ ክልሎች  20 የሚደርሱ ተቋራጮች በእጃቸው የሚገኘው የመንግስት ሃብትና ንብረት እንዲመልሱ መደረጉን አስረድተዋል፡፡

ሚኒስቴሩ ከክልል ጤና ጥበቃ ቢሮዎች ጋር በመሰረተው ፎረም አማካኝነት በተካሄደው ውይይት በአፈፃፀም አማራ እና  ሶማሌ ክልል የተሻሉ ሆነው ተገኝተዋል ።

በዝቅተኛ አፈጻጻም ደግሞ የደቡብ ክልል ተጠቅሷል ።

ችግሮችን በመለየት ሁሉም  ክልሎች በተመጣጣኝ የአፈጻጻም ደረጃ ላይ ለማድረስ የሚያስችል ጥናትና እቅድ ተዘጋጅቶ ወደ ስራ መገባቱን  አቶ ታደሰ ጠቁመዋል፡፡

በደቡብ ክልል ጤና ቢሮ የጤና ፕሮጀክቶች ማስፋፊያ ግንባታ አስተባባሪ  አቶ ሳሚኤል ሸሪፎ በበኩላቸው በጤና ተቋማት  ጥራት ያለው አገልግሎት ለመስጠት የሚያስችል  የውሃና የኃይል አቅርቦት ችግር በዘርፉ ፈተና እየሆነ መምጣቱን ተናግረዋል፡፡

"በክልሉ የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል ግንባታ አርባ ሶስት በመቶ ላይ የሚገኝ መሆኑን ስንመለከት  ያለው አፈጻጻም  ዝቅተኛ በመሆኑ መሻሻል የሚገባው ነው" ብለዋል፡፡

ለአፈጻጸሙ ዝቅተኛ መሆን ምክንያቱ የሰው ኃይል አደረጃጀት ሲሆን በተለይም በክልሉ ጤና ቢሮ ያለው የመሃንዲስ ቁጥር ከ3 ያልበለጡ መሆናቸው ይጠቀሳል ።

በተጨማሪም  በክልሉ ያለው የጸጥታ ችግር በጤና ተቋማት ግንባታ ላይ ተጽእኖ እንዳደረገም ገልጸዋል፡፡

" ክልሉ ካለው የህዝብ ብዛት አንጻር የጤና ተቋማት በቂ ባይሆንም በእቅድ ተይዘው ወደ ግንባታ ሂደት የተገቡትን በተሻለ ጥራትና ፍጥነት በማጠናቀቅ አገልግሎት እንዲሰጡ  እየተደረገ ነው" ያሉት ደግሞ በአማራ ክልል ጤና ጥበቃ ቢሮ የሲቪል ምህንድስና ባለሙያ  አቶ ዘሩ ደመቀ ናቸው፡፡

በክልል  የሰው ኃይል አደረጃጀት የተሻለ መሆኑን የተናገሩት አቶ ዘሩ አርባ ሁለት  የሚደርሱ በተለያዩ የምህንድስና ዘርፍ የሚያገለግሉ ባለሙያዎች እንዳሉም ጠቁመዋል።

ውይይቱ  " የጤና ተቋማት ግንባታ ጥራት ላለው ህክምና ወሳኝ ነው"  በሚል መሪ ሃሳብ ለአራት ቀናት የተካሄደ  ሲሆን  ከፌዴራልና ክልሎች የተወጣጡ የዘርፉ ስራ ኃላፊዎችና ባለሙያዎች ተሳትፈዋል፡፡

ተሳታፊዎቹ በጅማ ከተማና አካባቢው የሚገኙ የጤና ተቋማትን እንቅስቃሴ ተመልክተዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም