ጠንክረን በመስራታችን ሀብት ማፍራት ችለናል— በአምቦ በማህበር የተደራጁ ወጣቶች

365

አምቦ የካቲት13/2011 መንግስት ባደረገላቸው ድጋፍ ተደራጅተው ወደ ስራ በመግባት ሀብት ከማፍራት ባለፈ ለሌሎች የስራ እድል መፍጠራቸውን በአምቦ ከተማ ወጣቶች ገለፁ።

በከተማው ታጀበና ጓደኞቹ እንጨትና ብረታ ብረት ስራ ማህበር ሰብሳቢ ወጣት ታጀበ አለማየሁ “ስድስት የማህበሩ አባላት ከአምስት ዓመት በፊት ከመንግስት በተሰጠን 300 ሺህ ብር ብድር በመታገዝ ወደ ስራ ገብተናል ” ብሏል።

“ጠንክረን በመስራታችን አሁን ላይ ካፒታላችን 5 ሚሊዮን ብር ደርሷል” ያለው ወጣት ታጀበ ለሌሎች 15 ወጣቶች የስራ እድል መፍጠራቸውን ገልጿል።

ስድስት የማህበሩ አባላት በነብስ ወከፍ የመኖሪያ ቤት መገንባታቸውን የገለፀው ወጣቱ የስራ ዘርፋቸውን ለማሰፋፋት ሁለገብ ህንጻ ለመገንባት ዝግጅት እያደረጉ መሆናቸውን አመላክቷል።

በተመሳሳይ የስራ መስክ የተሰማሩት የመሳይና ጓደኞቹ ማህበር አባላትም ጠንክረው በመስራታቸው ለውጤት መብቃታቸውን ገልፀዋል ።

ሰባት የማህበሩ አባላት ከስድስት ዓመት በፊት በብድር ባገኙት 200 ሺህ ብር መነሻ ካፒታል በጀመሩት ሰራ አሁን ላይ ለሌሎች 13 ወጣቶች የስራ እድል መፍጠራቸውን የማህበሩ ሰብሳቢ  ወጣት መሳይ አሳምናው ተናግሯል ።

እንደ ወጣት መሳይ ገለጻ የማህበራቸው ካፒታልም 3 ሚሊዮን ብር ደርሷል ።

በኦሮሚያ ብድርና ቁጠባ ተቋም የምዕራብ ሸዋ ዞን ጽህፈት ቤት ስራ አስኪያጅ አቶ ዳምጠው አለማየሁ ባለፉት ሰባት ወራት ተደራጅተው ወደ ተቋሙ ለመጡ 11 ሺህ ደንበኞች 102 ሚሊዮን ብር ብድር ማመቻቸቱን ተናግረዋል ።

ወጣቶቹ በብድር ገንዘቡ በመታገዝ በከብት ማድለብ፣ መስኖ ልማት፣ ብረታ ብረትና እንጨት ስራ እንዲሁም በአነስተኛና ጥቃቅን ንግድ ስራ መሰማራታቸውን አስረድተዋል።

ስራ አስኪያጁ እንዳሉት ባለፉት ወራት 135 ሺህ የተቋሙ ደንበኞች 181 ሚሊዮን ብር  ቆጥበዋል ።

ከዞኑ የስራ ዕድል ፈጠራ ጽህፈት ቤት የተገኘው መረጃ መሰረት በጀት ዓመቱ 25ሺህ የሚሆኑ ወጣቶችን ወደ ስራ ለማሰማራት ታቅዶ በግማሽ ዓመቱ 13ሺህ 100 ተጠቃሚ ማድረግ ተችሏል።