የዞኑ የስፖርት ምክር ቤት ከአንድ ሚሊዮን ብር በላይ በጀት አጸደቀ

56

አምቦ የካቲት 13/2011 የምዕራብ ሸዋ ዞን ስፖርት ምክር ቤት ትናንት ባካሄደው 22ኛ መደበኛ ጉባኤው የስፖርቱን ዘርፍ ለማጠናከር የሚያግዝ 1 ሚሊዮን 200 ሺህ ብር በጀት አጸደቀ፡፡

የስፖርት ምክር ቤቱ ሰብሳቢና የዞኑ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ገዛኸኝ ከበደ በጉባኤው ላይ እንደገለጹት በሁሉም የስፖርት ዘርፎች የህዝብ ተሳትፎ እያደገ መጥቷል።

ይህን የህዝብ ተሳትፎ  አጠናክሮ ለማስቀጠልና ስፖርቱን ለማሳደግ በዘንድሮ ዓመት የተለያዩ ተግባራት እንደሚከናወኑ ተናግረዋል።

አቶ ገዛኸኝ እንዳሉት ምክር ቤቱ ባጸደቀው በጀት በዞኑ ሁሉም ወረዳዎች የስፖርት ማዘውተሪያና መዝናኛ ስፍራዎችን ከማመቻቸት ባለፈ የተለያዩ ስልጠናዎች ይካሄዳሉ፡፡  

በተጨማሪም የታዳጊዎችን ተሳትፎ በማሳደግ ቀጣይነት ባለው መልኩ ተተኪዎችን ለማፍራት ፕሮጀክቶችንና የባህል ስፖርቶችን የማሳደግ ሥራ ትኩረት እንደሚሰጠው ነው የገለጹት።

በተለያየ ጊዜ ህዝቡ የሚያነሳቸውን ጥያቄዎች ለመመለስ ባለሃብቶችና የከፍተኛ ትምህርት ተቋማትን በዘርፉ አሳትፎ ለመስራት የተለያዩ ተግባራት መጀመራቸውንም አመልክተዋል፡፡

የስፖርት ምክር ቤቱ ጸሐፊ አቶ አበራ ጌታቸው በበኩላቸው "በዞኑ በስፖርቱ ዘርፍ የህዝቡ ተሳትፎና ተጠቃሚነት እያደገ ቢመጣም ከፍላጎትጋር ለማጣጣም ተጨማሪ ስራዎችን መስራት ያስፈለግላል" ብለዋል፡፡

ስፖርት ጤናማና ምርታማ ዜጋን ለማፍራት ያለው ፋይዳ ከፍተኛ በመሆኑ ዘርፉን ለማጠናከር አቅምን አሟጦ መስራት እንደሚገባ ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም