ሚኒስቴሩ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የምርምር ስራዎችን እየደገፈ መሆኑን ገለጸ

92

ደብረብርሀን የካቲት 13/2011 በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የሚካሄዱ የምርምር ስራዎች የህብረተሰቡን መሰረታዊ ችግር የሚፈቱ እንዲሆኑ እየደገፈ  መሆኑን የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡

ደብረብርሃን ዩኒቨርስቲ ባለፉት ሦስት ዓመታት ምርምር ሲያደርግበት የነበረውን የተቀናጀ የግብርና ጥናትና ምርምር ማዕከል ተመርቆ ለተጠቃሚዎች አስተላልፏል፡፡  

ማዕከሉ ለተጠቃሚዎች በተላለፈበት ስነስርዓት ወቅት የተገኙት የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትሩ ዶክተር ኢንጅነር ጌታሁን መኩሪያ እንዳሉት በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የሚካሄዱ ምርምሮች ተለይተው የህዝብ ችግሮችን ሊፈቱ ይገባል፡፡

ከተለያዩ ዩኒቨርስቲዎች ተመርጠው እየተካሄዱ ላሉ ከ60 በላይ የምርምር ስራዎች የ300 ሚሊየን ብር ድጋፍ መደረጉን አስታውቀዋል፡፡

የደብረብርሃን ዩኒቨርስቲ ከሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ጋር ተቀናጅቶ ከጀመራቸው የጥናትና ምርምር ስራዎች መካከል የተቀናጀ የግብርና ጥናትና ምርምር አንዱ እንደሆነም  አመልክተዋል፡፡

የምርምር ማዕከሉ ዓሳ፣ ዶሮ እና የጓሮ አትክልት በአነስተኛ መሬት በማልማት በአጭር ጊዜ ውሰጥ ሀብት በማመንጨት የምግብ ዋስትና ለማረጋገጥ የሚያግዝ  ውጤታማ ስራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

የምርምሩ ውጤቶች በአነስተኛ መሬት  በሁሉም ሰው አቅም እንደሚሰራ የገለጹት ሚኒስትሩ ምርምሩ በሌሎች የክልሉ አካባቢዎች እንዲስፋፋም የትግበራ መመሪያ ለአማራ ክልል መንግስት እንዲደርስ መደረጉን ጠቅሰዋል፡፡

በደብረብርሃን ዩኒቨርስቲ የጥናትና ምርምር ማህበረሰብ አገልግሎት ምክትል ፕሬዚዳንት ዶክተር አልማዝ አፈራ በበኩላቸው በኤፍራታና ግድም ወረደ በዩሙሎ ቀበሌ ለተከናወነው ጥናትና ምርምር ፕሮጀክት 930 ሺህ ብር ወጪ መደረጉን ተናግረዋል፡፡

የምርምር ውጤት የሆነው ማዕከሉም ከአረብ ሀገር የተመለሱ ሰባት የአካባቢው ወጣቶች አደራጅቶ በማሰማራት ተጠቃሚ ማድረግ ጀምሯል፡፡

ፕሮጀከቱም በየአካባቢው አለአገባብ ይባክን የነበረውን አነስተኛ  መሬት፣ ውሃና ተረፈ ምርት  አቀናጅቶ ወደ ሀብት መቀየር የተቻለበትና  ጠቀሜታው ከፍተኛ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡

ሴቶች ፣ ወጣቶችና አረጋዊያንን በማሳተፍ የሚሰራው ፕሮጀክቱ የሚያስገኘው ገቢ የላቀ እንደሆነም አስረድተዋል፡፡

በቀጣይም በክልሉ ካሉ ዩንቨርስቲዎች ጋር በመነጋገር ለማስፋት እንደሚሰራ ጠቁመው፤ የኢኖቨሽንና ቴክኖለጂ ሚኒስቴር በሚያደርገው የገንዘብ ድጋፍ በተጨማሪ በአኮበር ወረዳ የመድኃኒት ቅመማ ፕሮጀክት ምርምር በመጠናቀቅ ላይ እንደሚገኝ ጠቁመዋል፡፡

ዩኒቨርስቲው በሚያካሂደው  ምርምር በአካባቢ ጥበቃና በሌሎችም የልማት ዘርፎች ህብረተሰቡን እየደገፈ እንደሚገኝ የተናገሩት ደግሞ የሰሜን ሸዋ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ተፈራ ወንድም አገኘሁ ናቸው፡፡ 

ፕሮጀክቱ  ፈጥኖ ወደ ሌሎች ወረዳዎችና ከተማ አስተዳደሮች በማስፋት ለህብረተሰቡ ተጠቃሚነት እንደሚሰራም አስታውቀዋል፡፡

በፕሮጀክቱ ከታቀፉት  ወጣቶች መካከል መሀመድ ሸህ አሊ በሰጠው አስተያየት ተደራጅተው" ሎማን " የተባሉ 100 የዶሮ ዝርያዎችን በማስመጣት በቀን 80 እንቁላል መጣል እንደሚችሉ በተግባር መረጋገጣቸውን ገልጿል፡፡

እንቁላሉን በመሸጥ በአጭር ጊዜ ውስጥ ከ40 ሺህ ብር መቆጠብ እንደቻሉ ተናግሯል፡፡

በአካባቢው አርሶ አደሮችም እነሱን በመመልክት በዶሮ እርባታው በመሳተፍ ላይ እንደሆኑ ጠቁሞ ፕሮጀከቱ ከዚህ በፊት በአካባቢያቸው በምግብነት የማይታወቀውን ዓሳ የመመገብ ባህል የማላመድ ስራ እየካሄደ እንደሚገኝ አመልክቷል፡፡

ማዕከሉ በአካባቢው ለሚገኙ ተጠቃሚዎች በተላለፈበት ስነስርዓት የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ፣ የዩኒቨርስቲው  ማህበረሰብና የአካባቢው ነዋሪዎች እንዲሁም ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም