ለኢትዮጵያና ኤርትራ ዘላቂ ሰላምና ፍቅር የህዝብ ለህዝብ ግንኙነቱ ወሳኝ ነው---የደቡብ ክልል ምክር ቤት

96

ሀዋሳ የካቲት 12/2011  የኢትዮጵያና የኤርትራ ህዝቦች ለሰላምና ለፍቅር ላላቸው ጥልቅ ፍላጎት አሁን የተፈጠረው የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት ወሳኝ ማሳያ እንደሆነ የደቡብ ክልል ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ አስታወቁ።

የኤርትራ ፐብሊክ ዲፕሎማሲ የባህል ልዑካን ቡድን ዛሬ በሀዋሳ የኪነጥበብ ስራዎቹን አቀረበ።

በስነ-ስርዓቱ ላይ የተገኙት የክልሉ ምክር ቤት ዋና አፈጉባኤ ወይዘሮ ሄለን ደበበ እንዳሉት ባለፉት ሁለት አስርት ዓመታት በሁለቱ ሀገራት መካከል ተፈጥሮ የነበረው ጦርነትና አለመግባባት ወንድማማች ህዝቦችን አለያይቶ ቆይቷል።

ይህ የታሪክ ጠባሳ ሳያግዳቸው ሁለቱም ህዝቦች በተራራቁባቸው ዓመታት ለሰላምና ለፍቅር ያላቸውን ጥማት ሲገልጹ እንደነበርና ሀገራቱ የሚያቀራርብና የሚያገናኝ ለውጥ እንደሚመጣ በተስፋ ሲጠብቁ እንደነበር ገልጸዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ በበዓለ ሲመታቸው በገቡት ቃል መሰረት ሁለቱን ህዝቦች የለያቸውን ግድግዳ አፍርሰው በመሪዎችና በመንግስት ደረጃ የተጀመረው ግንኙነት ዛሬ ለደረሰበት የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት መሰረት መጣሉን ተናግረዋል።

ኤርትራዊያንን ቱባ ባህላቸውንና ማራኪ አጨፋፈራቸውን ማቅረባቸው የህዝብ ለህዝብ ትስስሩን ለማጠናከር የተጀመረውን ተልዕኮ ዳር ለማድረስ የሚያስችል የመጀመሪያ እርምጃ እንደሆነ ጠቁመዋል።

“ወደ ኤርትራ በሚጓዘው የኢትዮጵያ ፐብሊክ ዲፕሎማሲ ቡድን የመካተት እድሉን ካገኘን የክልላችን የባህል አምባሳደር የኪነ-ጥበብ ባለሙያዎች በአስመራ ተገኝተው የክልላችንን ቱባ ባህልና የአጨፋፈር ስልት ለህዝባችሁ የማቅረብ ፍላጎት አለን” ብለዋል።

በአፍሪካ ህብረት የኤርትራ ተወካይ የሆኑት አምባሳደር አርአያ ደስታ በበኩላቸው እንዳሉት የባህል ቡድኑ ወደ ሀዋሳ ከተማ ከገባበት ጊዜ አንስቶ ህዝቡ ባደረገላቸው አቀባበል የተሰማቸውን ደስታ ገልጸዋል።

“የሁለቱ ሀገራት ህዝቦች እርስ በእርስ የተወራረሰ ባህል ያላቸው መሆናቸውን የክልሉ ባህል ቡድን ባቀረበው ዝግጅት ላይ የተመለከትነው የአጨፋፈር ስርዓት የሚያሳይ ነው” ብለዋል።

የኤርትራ የባህል ቡድን ትርኢቱን በኢትዮጵያ ከተሞች ካቀረበ ረጅም አመታት እንዳስቆጠረ የተናገሩት አምባሳደሩ በሁለቱ ህዝቦች መካከል የነበረው የመራራቅ ዘመን አክትሞ አዲስ የሰላም የመረዳዳትና የመተጋገዝ ጊዜ መምጣቱን ገልጸዋል።

“ፕሬዝዳንት ኢሳያስና ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ከልባቸው ባመኑበት መሰረት ቀደም ሲል የነበረውን ሰላም ፍቅርና መረዳዳትን በኤርትራና በኢትዮጵያ ህዝቦች መካከል ማምጣት እንደሚቻል አልጠራጠርም”ብለዋል።

በውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር የፐብሊክ ዲፕሎማሲ ዲያሬክቶሬት ዲያሬክተር አምባሳደር ሙሉጌታ ከሊል እንዳሉት በሁለቱ ህዝቦች መካከል ያለውን ትስስር ለማጠናከር መንግስት የተለያዩ ተግባራትን እያከናወነ ይገኛል።

ሁለቱ ሀገራት በኢኮኖሚው በማህበራዊና በፖለቲካው መስክ ያላቸውን ግንኙነት ለማጠናከር በዩኒቨርሲቲዎችና በከተሞች ጉድኝት በተለይ በአዲስ አበባና በአስመራ መካከል የእህት ከተሞች ግንኙነት ይመሰረታል ተብሎ እንደሚጠበቅ ገልጸዋል።

የኤርትራ የፐብሊክ ዲፕሎማሲ ልዑክ ከነገ በስቲያ ሀሙስ የመጨረሻውን ዝግጅት በአዲስ አበባ እንደሚያደርግም ተናግረዋል።

“በአዲስ አበባ በሚሊኒየም አዳራሽ ከቀኑ በ11 ሰዓት ጀምሮ 25 ሺህ የሚጠጋ የከተማው ነዋሪ የሚታደምበት የማጠቃለያ ኮንሰርት ከፍተኛ የመንግስት ሀላፊዎች ታላልቅ ሰዎች የሀይማኖት መሪዎች ይሳተፋሉ” ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም