በሕክምና ባለሙያዎች የሚታዘዙላቸውን መድኃኒት ለመጠቀም የዋጋ ልዩነት እየተፈታተናቸው መሆኑን ነዋሪዎቹ ገለጹ

65

ማይጨው የካቲት 12/2011 በሕክምና ባለሙያዎች የሚታዘዙላቸውን መድኃኒት ለመጠቀም የዋጋ ልዩነት  እየተፈታተናቸው  መሆኑን የትግራይ ደቡባዊ ዞን ሦስት ከተሞች ነዋሪዎች ገለጹ፡፡

የትግራይ ክልል ጤና ቢሮ በበኩሉ በጤና ተቋማት የሚታየውን የመድኃኒት አያያዝና አጠቃቀም ሥርዓት ለማሻሻል እየሰራሁ ነው ብሏል፡፡

ከከተሞቹ ነዋሪዎች አንዳንዶቹ  ለኢ ዜ አ እንዳስታወቁት በመንግሥት ሆስፒታሎች በተመጣጣኝ ዋጋ ይቀርቡላቸው የነበሩትን መድኃኒት ባለማግኘታቸው ከአቅማቸው በላይ ወጪ በማድረግ ለመግዛት ተገደዋል።

በአላማጣ ሆስፒታል በ200 ብር ይቀርብላቸው የነበረውን የስኳር በሽታ መድኃኒት ከግል መድኃኒት ቤት በ400 ብር በመግዛት እየተጠቀሙ መሆናቸውን የከተማው ነዋሪ አቶ መኮንን ይሄይስ ይገልጻሉ፡፡

የሚጥል በሽታ መድኃኒት በ150 ብር ይገዙ እንደነበር የሚናገሩት የመሆኒ ከተማ ነዋሪው አቶ ገብሩ ስዩም ከግል መድኃኒት መደብር በ350 መቶ ብር ገዝቼ እየተጠቀምኩ ነው ይላሉ።ዋጋውም  ወርኃዊ ገቢያቸው እየተፈታተነ መጥቷል ይላሉ፡፡

ከኮረም ሆስፒታል በተመጣጣኝ ዋጋ ያገኙት የነበረው የስኳር በሽታ መድኃኒት በ200 ብር ጭማሪ በመግዛት ላይ መሆናቸውን የሚናገሩት ደግሞ የኮረም ከተማ ነዋሪ ሼክ ኢብራሂም ሰዒድ ናቸው፡፡

ለመድኃኒቱ በወር የሚያወጡት 450 ብር ወጪውን መቋቋም እንዳላስቻላቸው ተናግረዋል፡፡

የአላማጣ አጠቃላይ ሆሰፒታል ሥራ አስኪያጅ አቶ ሓዱሽ  ኃይሉ ከክልሉ ጤና ቢሮ ለሆስፒታሉ የሚላከው መድኃኒት መቀነስ ለእጥረቱ ዋነኛ ምክንያት መሆኑን ገልጸዋል፡፡

የማይጨው ሆስፒታል ሥራ አስኪያጅ አቶ ኪዱ ተክሉ ሆስፒታሉ ከቢሮው የሚላክለት መድኃኒት መጠን እያነሰ በመምጣቱ የተገልጋዩን ፍላጎት ማሟላት እንዳልቻለ ተናግረዋል፡፡

ሆስፒታሉ በውስጥ ገቢው ተጠቅሞ እጥረቱን ለማቃለል ቢጥርም፤ ተፈላጊው መድኃኒት በአገር ውስጥ ገበያ ለማግኘት ችግር እንደሚያጋጥም አስታውቀዋል፡፡

የመሆኒ አጠቃላይ ሆስፒታል ሥራ አስኪያጅ  አቶ ጎይቶም ዓለሜ በበኩላቸው ከቢሮው ለሆስፒታሉ የሚቀርበው መድኃኒት ውሱንነት መሆኑ፣የበጀት እጥረትና የውስጥ ገቢ ማነስ እጥረቱን ለማቃለል እንዳላስቻላቸው ገልጸዋል፡፡

የትግራይ ክልል ጤና ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ተክላይ ወልደገብርኤል በበኩላቸው ለክልሉ ጤና ተቋማት የሚቀርበው መድኃኒት 80 በመቶው ከውጭ ተገዝቶ እንደሚገባና በአገር ደረጃ ባለው የምንዛሪ እጥረትም መድኃኒት ለማስገባት ባለመቻሉ እጥረት መፈጠሩን አስረድተዋል፡፡

በተቋማቱ የሚታየው የመድኃኒት አስተዳደር ጉድለትም ለእጥረቱ ሌላኛው ምክንያት ነው ብለዋል፡፡

''የተቋማቱ የመድኃኒት መረጃ አያያዝ ሥርዓት ደካማ ነው''ነው ያሉት አቶ ተክላይ፣በተቋማቱ የሚታየው የመድኃኒት ብክነት በአገር አቀፍ መለኪያ ከተቀመጠው ከሁለት በመቶ በላይ  መሆኑን በማስረጃነት አቅርበዋል።

ቢሮው እጥረቱን ለማቃለል በተቋማቱ አዲሱን የሕክምና አሰጣጥ ደረጃ ፕሮቶኮል መተግበር እንደጀመረ አስታውቀዋል፡፡

ፕሮቶኮሉ የመድኃኒት አስተዳደር ሥርዓትን በማሻሻል በግዢ፣ በማጓጓዝ፣ በክምችትና በስርጭት የሚያጋጥመውን ብክነት እንደሚያስቀር አቶ ጎይቶም አመልከተዋል፡፡

''በጣም ወሳኝ''ተብለው የተለዩ መድኃኒት ግዢና ስርጭት በመንግሥት የጤና ተቋማት እንደሚከናወን ያወሱት ምክትል ኃላፊው፣ ቢሮው የተወሰነ መድኃኒት ከውጭ ለማስገባት ግዢ  እየፈጸመ  መሆኑን አስታውቀዋል፡፡

በተቋማቱ የሚገኝ መድኃኒት ከአንዱ ወደሌላው በማዟዟር ጥቅም ላይ የሚውልበት አሰራር ይዘረጋል ብለዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም