በአርሶ አደሩ የሚዘጋጀው የተፈጥሮ ማዳበሪያ የጥራት ደረጃውን ያሟላ አይደለም... የጎንደር የአፈር ምርመራ ላቦራቶር ማዕከል

57

ጎንደር የካቲት 12/2011 በአርሶ አደሩ የሚዘጋጀው የተፈጥሮ ማዳበሪያ የጥራት ደረጃው በአብዛኛው አነስተኛ መሆኑን በተደረገ ፍተሻ ማረጋገጡን የጎንደር የአፈር ምርመራ ላቦራቶር ማዕከል አስታወቀ፡፡

የማዕከላዊ ጎንደር ግብርና መምሪያ በበኩሉ በተፈጥሮ ማዳበሪያ አዘገጃጀት ላይ የሚስተዋሉ የጥራት ችግሮችን ለመቅረፍ እየሰራሁ ነው ብሏል፡፡

የማዕከሉ ኃላፊ አቶ ታደሰ ደምሴ ለኢዜአ እንደተናገሩት በሰሜን፣ በደቡብ፣ በማዕከላዊና በምዕራብ ጎንደር ዞኖች በአርሶአደሩ የሚዘጋጀው የተፈጥሮ ማዳበሪያ የጥራት መስፈርቶችን ያላሟላ ነው፡፡

ማዕከሉ በመስክ ናሙናዎችን በማሰባሰብና በላቦራቶሪ ጭምር በመፈተሽ ባደረገው የጥራት ቁጥጥር አብዛኛው የተፈጥሮ ማዳበሪያ ደረጃውን ጠብቆ ያልተዘጋጀና ለሰብል ምርታማነት መጨመር ዝቅተኛ አስተዋጽኦ ያለው ነው፡፡

የተፈጥሮ ማዳበሪያ ከአመድ፣ ከከብቶች ፍግ፣ ከአረንጓዴ እጸዋቶችና ከሰብል ቅሬት የሚዘጋጅ ቢሆንም አርሶአደሩ እያዘጋጀ ያለው በአብዛኛው አመድ የበዛበት ሆኖ ተገኝቷል፡፡

"የተፈጥሮ ማዳበሪያ በቂ እርጥበትና ሙቀትን በማመጣጠን እንዲብላላ ተደርጎ መዘጋጀት አለበት" ያሉት ኃላፊው በመስክ ምልከታና ፍተሻ የተረጋገጠው ማዳበሪያ ከዚህ በተቃራኒው የተዘጋጀ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

የጥራት ደረጃውን ሳያሟላ ጥቅም ላይ እየዋለ የሚገኘው የተፈጥሮ ማዳበሪያ አረም በማብዛት፣ ሰብል በማጠውለግ፣ የቅጠሉን ቀለም ወደ ቢጫ በመቀየርና ፍሬ እንዳያፈራ በማድረግ በምርታማነት ላይ አሉታዊ ተጽእኖ መፍጠሩን ተናግረዋል፡፡

"በዞኖቹ በየአመቱ ከፍተኛ መጠን ያለው የተፈጥሮ ማዳበሪያ በአርሶ አደሩ እየተዘጋጀ ጥቅም ላይ እየዋለ ነው" ያሉት ኃላፊው በማዳበሪያ ዝግጅት ላይ የልማት ጣቢያ ሰራተኞች የቅርብ ክትትልና ድጋፍ ሊያደርጉ እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡

የማዕከላዊ ጎንደር ዞን የአፈር ለምነት ባለሙያ ተወካይ አቶ በሪሁን መልካሙ ታካች "አርሶ አደሮች ጥራቱን ያልጠበቀ የተፈጥሮ ማዳበሪያ እንደሚያዘጋጁ ማረጋገጥ ተችሏል" ብለዋል፡፡

በአሁኑ ወቅትም የልማት ጣቢያ ሰራተኞችንና ሞዴል አርሶ አደሮችን በማቀናጀት ጥራቱን የጠበቀና መስፈርቱን ያሟላ የተፈጥሮ ማዳበሪያ አዘገጃጀት ላይ በተግባር የተደገፈ ስልጠና እየተሰጠ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ባለሙያው እንዳሉት በዘንድሮ የበጋ ወራት በዞኑ በአርሶ አደሮች ይዘጋጃል የተባለውን 7 ሚሊዮን ሜትር ኪዩብ የተፈጥሮ ማዳበሪያ በጥራት ለማዘጋጀት ንቅናቄ ተጀምሯል፡፡

"እስካሁንም 5ሺህ ሄክታር መሬት ለማልማት የሚያስችል 2 ነጥብ 5 ሚሊዮን ሜትር ኪዩብ በአርሶአደሮች ተዘጋጅቷል" ብለዋል፡፡

በወገራ ወረዳ የጀጀህ ቀበሌ ነዋሪ አርሶአደር ማሩ አያሌው "የተፈጥሮ ማዳበሪያ የአፈር ለምነትን ጠብቆ ከማቆየት አንጻር ከሰው ሰራሽ ማዳበሪያ የተሻለ ሆኖ አግኝቼዋለሁ" ብለዋል፡፡

"ማዳበሪያው ለስንዴ፣ ለገብስ፣ ለባቄላና ለአተር ሰብሎች ተስማሚ ነው" ያሉት አርሶአደር ማሩ አዘገጃጀቱ አድካሚና ጉልበት የሚጠይቅ በመሆኑ ጥራቱ ተጠብቆ ይዘጋጃል ማለት እንደማይቻል ተናግረዋል፡፡

"ስለ ተፈጥሮ ማዳበሪያ አዘገጃጀት ስልጠና ባገኝም በግብአት አቅርቦት እጥረት ምክንያት ማዳበሪያውን ከአመድና ከከብቶች ፍግ ብቻ ነው የማዘጋጀው" ያሉት ደግሞ የእዚሁ ወረዳ ነዋሪ አርሶ አደር ቢያድግልኝ ሙሉአለም ናቸው፡፡

በማዕከላዊ ጎንደር ዞን ለ2011/12 የምርት ዘመን የሚውል የተፈጥሮ ማዳበሪያ ለማዘጋጀት ከአንድ ሚሊዮን በላይ አርሶ አደሮች በመሳተፍ ላይ እንደሚገኙ ከዞኑ ግብርና መምሪያ የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም