በኢትዮጵያ እግር ኳስ ክለቦች የሚጫወቱ የውጭ አገራት ዜጎች ዘርፉን እያሳደጉት ነውን?

844

አዲስ አበባ የካቲት 12/6/2011 በእግር ኳሱ ዓለም የሚታወቁ ሀገራት ክለቦች አሉ የሚባሉ ተጫዋቾችን በብዙ ሚሊዮን ዶላር ወጪ ከሌሎች ሀገራት ክለቦች  መግዛትና ማስፈረም በየእለቱ የሚደመጥ የተለመደ ዜና ነው።

እነዚህ ክለቦች በየአገሮቻቸው ካለው የስፖርቱ እድገት ባሻገር ዘርፉ በምጣኔ ኃብቱ ውስጥ በተለይም በሚዲያውና ማስታወቂያው ኢንዱስትሪ ሁነኛ ቦታ የተቆናጠጡ፤ ከቴሌቪዥን ቀጥታ ስርጭት፣ ማስታወቂያና ስፖንሰርሺፕ ክፍያ የገንዘብ አቅማቸውን ያፈረጠሙ ናቸው።

እነዚህ ክለቦች ተጫዋቾችን እያጫረቱ ጭምር የሚገዙትም በኢንዱስትሪው ውስጥ ያለውን ምጣኔ ኃብታዊ ትርፍ ለመሳበ በሚል መሆኑም ይታወቃል።

ሆኖም ይህን የመሰለ እግር ኳስና ተያያዥ ኢንዱስትሪ በሌለባት ኢትዮጵያ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ክለቦች በከፍተኛ ወጪ የውጭ አገር ዜጋ የሆኑ ተጫዋቾችን ማስፈረም ጀምረዋል።

ይህም በብዙ የስፖርት ቤተሰብ ዘንድ አነጋጋሪ እየሆነ ነው።

አንዳንዶች የኢትዮጵያ ክለቦች የውጭ አገር ተጫዋቾችን የሚቀጥሩት የክለባቸውን ውጤታማነት ለማጠናከርና የዋንጫ ባለቤት ለማድረግ እንደሆነ ይገልፃሉ።

ሌሎች ደግሞ የውጭ ተጫዎቾች እየበዙ የመጡት ክለቦች አላስፋላጊ ፍክክር ውስጥ በመግባታቸው ነው ይላሉ።

እንዲያም ሆኖ የውጭ ተጫዋቾች  ለሀገሪቱ እግር ኳስ ማደግ የሚያበረከቱት አስተዋጽኦ እዚህ ግባ የሚባል አይደለም ይላሉ የኢትዮጵያ ቡና ስፖርት ክለብ ስራ አስኪያጅ አቶ ስንታየሁ በቀለ። 

በአሁኑ ወቅት ከግብ ጠባቂ ጀምሮ በአጥቂና ተከላካይ ቦታዎች የውጭ ተጫዋቾች እየተበራከቱ መሆኑን የሚናገሩት አቶ ስንታየሁ “ይህም የሆነው ክለቦች ከታች ያሉ ታዳጊዎች ላይ ከመስራት ይልቅ በማይጠቅም ፉክክር ውስጥ በመግባታቸው ምክንያት የመጣ ችግር ነው” ብለዋል።

ክለቦች ያላቸውን ውስን ኃብት ብዙም ለማያስፈለግ ተግባር ከማዋል ይልቅ ታዳጊዎችን ማፍራት ለሚያስችሉ የሰልጠና መርሃ ግብሮች ቢያወሉት ይመረጣል ባይ ናቸው።  

የኮንስራክሽን ስራዎች ኮርፖሬሽን እግር ኳስ ክለብ ስራ አስኪያጅ አቶ አሸናፊ እጅጉ በበኩላቸው በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያ ክለቦች ውስጥ እየተጫወቱ ያሉት አብዛኛዎቹ የውጭ ተጫዎች ያላቸው ችሎታ ከአገር ውስጥ ተጫዋቾች የተሻለ አይደለም ይላሉ።

“ከውጭ አገር የሚቀጠሩት ተጫዋቾች ብዙም ተወዳዳሪ ያልሆኑና የተለየ ብቃት ያላቸው አይደሉም” ብለዋል።  

የውጭ ተጫዋቾችን የመቅጠር ዓላማ የአገር ውስጥ እግር ኳስን ለማሳደግ የሚያስችል ልምድ ለማሻገር ከሆነ በአቅም ደረጃ ከአገር ውስጥ ተጫዋቾች የተሻሉ መሆን እንደሚገባቸው ነው የተናገሩት።

የቅዱስ ጊዮርጊስ ስፖርት ክለብ  የቦርድ ሊቀመንበር አቶ አብነት ገብረመስቀል ከዚህ የተለየ ሀሳበ ያቀርባሉ።

የውጭ ተጫዋቾችን ወደአገር ቤት ማስመጣት ከመግታት በፊት በቂ ተጫዎቾችን በአገር ውስጥ ለማፍራት የሚያስችሉ አካዳሚዎችን መፍጠር  ላይ ቅድሚያ ተሰጥቶ ሊሰራ ይገባል ብለዋል።

በኢትዮጵያ ያሉ የውጭ ተጫዎች በአፍሪካ ደረጃ ለሚወዳደሩ ክለቦች ብዙ ርቀት መሄድ ባይችሉ እንኳ ቢያንስ በሰፊ ጎል ልዩነት ከመሸነፍ እየታደጉን ነው ነው የሚሉት አቶ አብነት ከዚህ በተጨማሪ ሊጉ የተሻለ ድምቀት እንዲኖረውም እያደረጉ ነው በማለት ይገልፃሉ።

”ሆኖም ወደአገራችን ከለቦች የሚመጡ የውጭ አገራት ተጫዋቾች ሲመለመሉ ከኛ ተጫዎቾች የተሻሉ መሆን አለባቸው የሚለው ግን ያሳማማናል” ብለዋል።

የአዳማ ከተማ እግር ኳስ ክለብ ስራ አስኪያጅ አቶ አንበሴ መገርሳ ትልቁ ችግር ያለው ክለቦች መስራት ያለባቸውን የቤት ስራ ባለመስራታቸው ነው ይላሉ።

እርሳቸው እንደሚሉት በአሁኑ ወቅት እግር ኳስን ለማሳደግ ቁልፍ ሚና ይኖረዋል ተብሎ በሚታሰበው የታዳጊዎች ፕሮጀክት ላይ የሚሰራው ስራ የይምስል ነው።

“ታዳጊዎች የእግር ኳስ ተጫዎች ማፍራት ላይ  ከተሰራ  አማራጮች በመፍጠር ወደ ውጭ ከማማተር መታደግ ይቻላል” ሲሉም መክረዋል።

የኢትዮጵያ  እግር ኳስ ፌዴሬሽን በበኩሉ ወደ ኢትዮጵያ የሚመጡ የውጭ አገራት እግር ኳስ ተጫዎቾችን ከመቅጠር ጋር በተያያዘ ያለውን  መመሪያ  የማሻሻል ሀሳብ መኖሩን አስታወቋል።

የፌዴሬሽኑ ምክተል ፕሬዚዳንተ ኮሎኔል አወል አብዱረሂም እንደገለፁት በመመሪያው በተለይ የተጫዋቾች የብዛት ወሰንንና  የውጭ ዜጋ ማስፈረም የሚችለው የትኛው ሊግ ነው በሚለው ላይ ወደፊት ለውጥ ሊደረግ ይችላል። 

ይህም አስከሚቀጥለው ጠቅላላ ጉባኤ ድረስ ተሰርቶ በጉባኤው ከጸደቀ በኋላ በመጪው ዓመት ወደ ስራ የሚገባ ይሆናል ብለዋል።


አሁን ባለው የፌዴሬሽኑ መመሪያ መሰረት ክለቦች እስከ አምስት የሚደርሱ ተጫዎቾች ማስፈረም  የሚችሉ ሲሆን በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ከሚካፈሉ 16 ክለቦች መካከል ከወላይታ ዲቻና ከመከላከያ እግር ኳስ ክለብ በቀር ሁሉም ክለቦች ከአንድ እስከ አምስት የሚደርሱ የውጭ ተጫዎቾች አሏቸው።

ብዙዎቹ ተጫዎችም በአጥቂ ቦታ ላይ የሚጫወቱ ቢሆንም የፕሪሚየር ሊጉን  ኮከብ አግቢነት እስከ ሰባተኛ ያለውን ደረጃ  ኢትዮጵያን ተጫዎቾች እየመሩት ነው።

ይህም ከውጭ ወደ ኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊጉ መጥተው የሚጫወቱ በአቅም ከኢትዮጵያን የተሻሉ እንዳልሆነ አንዱ ማሳያ ነው የሚሉም አሉ።