የታሪክ ቅብብሎሹና ትውልዱ

166

አዲስ አበባ የካቲት 12/2011የካቲት 12 ቀን 1929 ዓ.ም በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ ጥቁር ጠባሳ ጥለው ካለፉ እለታት መካከል በዋናነት ይጠቀሳል።

በወቅቱ ወራሪው ፋሽስት ኢጣሊያን የጦር አዛዥ ሩዶልፍ ጊራዚያኒ በያኔው ገነተ ልዑል ቤተመንግስት በአሁኑ ስድስት ኪሎ ዩኒቨርሲቲ  ዲስኩር እያቀረበ ባለበት ወቅት ሞገስ አስግዶም አና አብርሃም ደቦጭ በተባሉ ኢትዮጵያውያን በተወረወረ ቦንብ ጉዳት ደረሰበት።

ጉዳቱን ተከትሎም ከ30 ሺህ የሚበልጡ የአዲስ አበባ ነዋሪዎች በግፍ የተጨፈጨፉ ሲሆን፤ ለመግደል  የሚፈለገው መስፈርት በመንገድ ላይ የተገኘ ማንኛውም ኢትዮጵያዊ መሆን እንደነበር የታሪክ ድርሳናት ያስረዳሉ።

እለቱ ዛሬ ስድስት ኪሎ በሚገኘው የሰማዕታት ሐውልት ታስቦ  የዋለ ሲሆን፤ ጉዳዩ ለአርበኞች ብቻ የተተወ እስኪመስል በበርካታ ጀግኖች አርበኞችና በጣት በሚቆጠሩ ወጣቶችና ህጻናት ተማሪዎች ተከብሯል።

ኢዜአ በዓሉን ለማክበር በስፍራው የታደሙ ህጻናት ተማሪዎችን "የካቲት 12 ለምን ይከበራል?" ሲል አነጋግሯቸዋል።

ተማሪዎቹ በሰጡት ምላሽ እለቱ የሰማዕታት ቀን ከመሆኑ ባለፈ ታሪኩን በደንብ ያስተማራቸው ሰው እንደሌለ ታዝበናል።

እለቱን ለማሰብ በስፍራው ከታደሙ ጥቂት ወጣቶች መካካል አንዷ የሆነችው ማርታ መንግስቱ በበኩሏ "በትምህርት ቤት ቆይታዬ ሰለ እለቱ ምንም ሲባል ሰምቼ አላውቅም" ስትል ትናገራለች።

ወጣቶች ታሪካቸውን ዞር ብላው መፈተሽ አንዳለባቸው በማውሳት።

የአሁኑ ትውልድ ለእሱ ሲባል የተከፈለውን መስዋትነት በማስታወስ ታሪክ እንዳይወቅሰው የሚጠበቅበትን ኃላፊነት መወጣት አንዳለበት የተናገረው ደግሞ ወጣት ነቢል ሲራጅ  ነው።

የጥንታዊ ጀግኖች አርበኞች ማህበር አባል የሆኑት ውይዘሮ ጽጌ ደምሴ የእለቱ አከባባር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተቀዛቀዘ መምጣቱን አስታውሰው፤ ትውለዱ ታሪኩን አንዲያውቅ ከትምህርት ቤት ጀምሮ ማስተማር እንደሚገባ ጠቁመዋል።

ሌላኛው የማህበሩ አባል አቶ የትባዬ ተስፋዬ መንግስት ለአገር ባለውለታዎች ተገቢውን ክብር አለመስጠቱ ወጣቶች ለታሪካቸው ትኩረት እንዳይኖራቸው ማድረጉን ይናገራሉ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም