የጤና ሚኒስቴር ካስገነባቸው 10 የህክምና መሳሪያዎች የጥገና ማዕከላት መካከል አራቱ ወደ ስራ መግባታቸውን ገለጸ

88

አዲስ አበባ የካቲት 12/2011 የጤና ሚኒስቴር ካስገነባቸው 10 የህክምና መሳሪያዎች የጥገና ማዕከላት መካከል አራቱን በመጀመሪያ የ100 ቀናት የዕቅድ ጊዜ ውስጥ ወደ ስራ እንዲገቡ ማድረጉን ገለጸ።

በመላ አገሪቱ ባሉ የህክምና ተቋማት 50 በመቶ የሚሆኑት የህክምና አገልግሎት መስጫ መሳሪያዎች በአግባቡ ጥቅም ላይ እየዋሉ አይደለም ተብሏል።

በኢትዮጵያ በውድ ዋጋ ተገዝተው ከውጭ የሚገቡ የህክምና መሳሪያዎች በአግባቡ ጥቅም ላይ እንዲውሉ ለማስቻል 10 የህክምና መሳሪያዎች የጥገና ማዕከላት (Biomedical workshop) መገንባቱን የጤና ሚኒስቴር አስታውቀዋል።

በጤና ሚኒስቴር የህክምና አገልግሎት ዳይሬክተር ጀነራል ዶክተር ያዕቆብ ሰማን ለኢዜአ እንዳሉት፤ ግንባታቸው የተጠናቀቁት የጥገና ማዕከላት መካከል የአዲስ አበባ፣ ሀዋሳ፣ መቀሌና ነቀምት ያሉት በመጀመሪያው የመቶ ቀን እቅድ ወደ ስራ ገብተዋል።

በሁለተኛው የመቶ ቀን እቅድ የሰመራ፣ ድሬዳዋ፣ ጅማና አሶሳ የጥገና ማዕከላት ስራ እንደሚገቡም ጠቁመዋል።

ቀሪዎቹ ሁለት የህክምና መሳሪያ የጥገና ማዕከላት በበጀት ዓመቱ መጠናቀቂያ ወደ ስራ እንደሚገቡ አመልክተዋል።

እንደ አገር የባዮሜዲካል ምህንድስና የትምህርት ዘርፍ የዳበረ ባለመሆኑ መሳሪያዎች በቀላሉ እንዳይበላሹ የማድረግ አቅም ውስን ነው።

በአንዳንድ የህክምና ተቋማት ባለሙያዎች ቢኖሩም ትልልቅ የህክምና መሳሪያዎችን መጠገን የሚችሉ ማዕከላት እንዳልነበሩ ገልጸዋል።

''በመሆኑም ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ችግሩን ለመፍታት በቅድሚያ የህክምና መሳሪያዎች በቀላሉ ስራ እንዲጀምሩ የሚያስችሉ 10 የጥገና ማዕከላት ተገንብተዋል'' ብለዋል።

ዓለም አቀፍ ልምድ ካላቸው ተቋማት ጋር በመተባበር የአቅም ማጎልበቻ ስልጠና እየተሰጠ እንደሚገኝ የገለጹት ዶክተር ያዕቆብ በህክምና መሳሪያዎች አጠቃቀምና አያያዝ ዙሪያ ስልጠና የሚሰጡ ተቋማት የአገልግሎት ዘመናቸውን ሲጨርሱ ስልጠናው ቀጣይነት እንዲኖረው ሚኒስቴሩ የራሱን ቡድን አቋቁሞ እየሰራ መሆኑን ጠቁመዋል።

በመሆኑም ዓለም አቀፍ ልምድ ያላቸው ተቋማት በሚሰጡት ስልጠና የተገኘውን ልምድ በአግባቡ ቀምሮ መስራት የሚያስችል አደረጃጀት መፈጠሩን ተናግረዋል።

በኢትዮጵያ በመንግስት የህክምና ተቋማት የሚገኙ ትልልቅ የህክምና መሳሪያዎች በሚበላሹበት ወቅት ፈጣን የሆነ ጥገና የማይደረግላቸው በመሆኑ ተገልጋዩ ለተጨማሪ ወጪ የሚዳረግበት ዕድል ሰፊ እንደሆነ ይታወቃል።

የጥገና ማዕከላቱ የችግሩን መጠን ሊቀንሱት እንደሚችል ተስፋ ተደርጓል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም