ሆስፒታሉ የከንፈርና የላንቃ መሰንጠቅ ጉዳት ላለባቸው 32 ሰዎች ነጻ የቀዶ ሕክምና ሰጠ

86

ደብረማርቆስ የካቲት 11/2011 የደብረማርቆስ ሪፈራል ሆስፒታል በተፈጥሮ የከንፈርና የላንቃ መሰንጠቅ ጉዳት ላለባቸው 32 ሰዎች ነጻ የቀዶ ሕክምና መስጠቱን አስታወቀ።

የሆስፒታሉ ሥራ አስኪያጅ አቶ አዲሱ አበባው ለኢዜአ እንዳስታወቁት ባለፉት ሦስት ቀናት ሕክምናው የተሰጠው ከምስራቅና ምዕራብ ጎጃም እንዲሁም ከፊል አዊ ዞን አካባቢዎች ለመጡ የችግሩ ተጋላጮች ነው፡፡

በህክምናውም ብዙ ዓመታት በችግሩ ተጋላጭ እንደሆኑ የተለዩ ሰዎችን በሙሉ ማከም እንደተቻለም ተናግረዋል፡፡

በክልሉ ጤና ቢሮ ሐረር ኢትዮጵያ ፕሮጀክት አስተባባሪ አቶ ንጋቱ የሻምበል በበኩላቸው "በተፈጥሯቸው የላንቃና የከንፈር መሰንጠቅ ጉዳት ያለባቸውን ሰዎች ህክምና እንዲያገኙ እየተደረገ ነው" ብለዋል።

ሕክምናው በመደበኛ የጤና ተቋማት አገልግሎቱ ስለማይሰጥ የዳበረ ልምድና ግብአት ካላቸው በጎአድራጎት ድርጅቶች ጋር በመተባበር ሕክምናውን ተደራሽ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

አቶ ንጋቱ እንዳሉት ከሐምሌ ወር 2011 ዓ.ም ጀምሮ በተለያዩ የክልሉ ሆስፒታሎች በቅንጅት በተሰጠ የሕክምና አገልግሎት ከ130 በላይ ሰዎችን ተጠቃሚ ማድረግ ተችሏል፡፡

በደብረማርቆስ ሆስፒታል ብቻ ለ32 የችግሩ ተጠቂዎች የተሰጠው ነፃ የህክምና አገልግሎትም ከ250ሺህ ብር በላይ ግምት እንዳለው ተናግረዋል።

የላንቃና የከንፈር መሰንጠቅ ምግብን በአፍ ውስጥ ለማላወስ እንቅፋት ከመሆኑ በተጨማሪ ጥርስ ከመደበኛው አበቃቀል ውጭ እንዲበቅል በማድርግ የጆሮ ህመምና መሰል የጤና ችግር ያስከትላል።

" ማህበረሰቡ የአምላክ ቁጣ ነው በሚል የተሳሳተ አመለካከት የችግሩ ተጠቂዎችን ሲያገል ይስተዋላል " ያሉት አቶ ንጋቱ በእዚህም ማህበራዊ ሕይወታቸው ላይ ተጽዕኖ እየደረሰ መሆኑን ነው የገለጹት።

የህክምና አገልግሎቱን ካገኙት መካከል በደንበጫ ከተማ የጉሬዛ ዱር ቀበሌ ነዋሪ አቶ ያለለት ልኬው በበኩላቸው ሲወለዱ ጀምሮ ከንፈራቸው የተሰነጠቀ በመሆኑ ሀሳባቸውን በትክክል ለመግለጽ ተቸግረው መቆየታቸውን አስታውሰዋል፡፡

በዚህ ሁኔታ 23 ዓመት እንደቆዩ ገልጸው በእዚህም ከሰው ጋር ለመገናኘት ሃፍረት ይሰማቸው እንደነበረና አሁን ባገኙት ህክምና ይህ ችግራቸው መፈታቱን ተናግረዋል።

ከጎንቻ ሲሶ እነሴ ወረዳ የነቆይ ቀበሌ ነዋሪ ህጻን ያሳብናት ጥላሁን በበኩሏ በከንፈሯ መሰንጠቅ ምክንያት ጀምራው የነበረውን ትምህርት አቋርጣ በቤት ውስጥ ለመዋል ተገዳ እንደነበር ገልጻለች።

በቅርቡ በደብረማርቆስ ሪፈራል ስፒታል በተደረገላት ህክምና ችግሯ በመፈታቱ ያቋረጠችውን የሁለተኛ ክፍል ትምህርት ያለምንም ስጋት ለመቀጠል መነሳሳቷን አስታውቃለች።

በደብረማርቆስ ሪፈራል ሆስፒታል የተሰጠው ህክምና እስማይል ክሊንና ሀረር ኢትዮጵያ ከሚባሉ ግብረሰናይ ድርጅቶች በተደረገ የገንዘብ፣ የቁሳቁስና የባለሙያ ድጋፍ መሆኑ ታውቋል ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም