በአዲስ አበባ ቱሪዝምን ለማሳደግ የግል ዘርፉን ለማሳተፍ እየተሰራ መሆኑ ተገለጸ

181

አዲስ አበባ የካቲት 9/2011 በአዲስ አበባ ቱሪዝምን ለማሳደግ ታሪካዊ ቅርሶችን ለመጠበቅና ለመንከባከብ የግል ዘርፉን ለማሳተፍ የሚያስችል ስራ እየተሰራ መሆኑን የባህል ኪነጥበብና ቱሪዝም ቢሮ ገለጸ።

ቢሮው በ2011 የበጀት ዓመት የአጋማሽ ዓመት አፈጻጸሙን ከሁሉም ክፍለ ከተሞች የባህል ኪነጥበብና ቱሪዝም ጽህፈት ቤቶች ጋር በመሆን ገምግሟል።

በአዲስ አበባ ከተማ 448 የሚደርሱ ታሪካዊ ቦታዎችና ቅርሶች ተመዝግበው የሚገኙ ሲሆን ቅርሶቹን በማደስ ለቱሪዝም ዘርፉ ለማቅረብ በመንግስት አቅም ብቻ የሚቻል ባለመሆኑ ለግል ባለሃብቶችን ተሳታፊ ለማድረግ እንቅስቃሴ ተጀምሯል።

የቢሮው ምክትል ዋና ሃላፊ አቶ ስዩም ተመስገን እንደለጹት፣ ቅርሶችን በደንብ ለመንከባከብና ለቱሪዝም ዘርፉ ለማዋል ለባለሃብቱ አስተላልፎ የመስጠት የአሰራር ስርዓት ተዘርግቶ እየተሰራበት ነው።

በልደታ ክፍለ ከተማ የሚገኝ አንድ ቅርስ ቤት ለግል ባለሃብት ተሰጥቶ ወደ 5 ሚሊዮን ብር ወጪ ተደርጎበት የስዕል ማሳያ አዳራሽ በመሆን ጭምር እያገለገለ እንደሆነ ጠቁመዋል።

በቂርቆስ ክፍለ ከተማ ውስጥ የሚገኘው የደጃዝማች አያሌው ብሩ ቅርስ ቤት ለሞዴል ሊያ ከበደ ተሰጥቶ ሰፊ የሆነ የቱሪዝም ልማት ስራ እየተሰራበት ነው።

በየካ ክፍለ ከተማም የራስ ስዩም ቤት ይኖሩ የነበሩ ሰዎች ተለዋጭ ቤት እንዲያገኙ በማድረግ ቤቱን ለቱሪዝም ስራ ለማዋል እየተሰራ እንደሆነም ተገልጿል።

በቅርስ ጥበቃ ዙሪያ የተጠናከረ ስራ ለመስራት የሰው ኃይል እጥረት የሚስተዋልበትና መዋቅሩም ጠንካራ ባለመሆኑ ባለፉት ስድስት ወራት በሚፈለገው ልክ መስራት እንዳልተቻለ ጠቁመዋል።

በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ የሚገኙ ቅርስ ቤቶችን ባለሃብት በማፈላለግ ቅርሶቹ ጥበቃ እንዲደረግላቸውና ለቱሪዝም ዘርፉ እንዲውሉ ለማድረግ ከቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለስልጣን ጋር  ጥረት እየተደረገ እንደሆነ ተገልጿል።

''የቅርስ ባለይዞታ አንድ ጊዜ ቅርስ ተብሎ ከተመዘገበ በኋላ ሃላፊነቱን በመንግስት ላይ ብቻ የመጣል ሁኔታ አለ'' ያሉት አቶ ስዩም የግሉን ባለሃብት ግንዛቤ በመስጠት ተሳታፊ እንዲሆን ለማድረግ መስራት እንዳለበት ገልጸዋል።

አለም አቀፍ ተቋማትና የግሉ ባለሃብት በዘርፉ በማሳተፍ ለወጣቱም የስራ እድል ከመፍጠር አኳያ እየተሰራበት ነውም ብለዋል።

በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ የሚገኙ ታሪካዊ ቅርሶችና አሮጌ ቤቶች 30 በመቶ በሃይማኖት ተቋማት ስር 70 በመቶ ደግሞ በፌዴራል የቤቶች ኮርፖሬሽን እጅ ላይ እንደሚገኙ የጠቆሙት አቶ ስዩም 3 በቅርስነት የተያዙ ቤቶች ብቻ በከተማ አስተዳደሩ እጅ እንደሚገኙ አመልክተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም