በዞኖቹና በኮንታ ልዩ ወረዳ የማህበራዊ ጤና መድህን አፈጻጸም ዝቅተኛ መሆኑ ተጠቆመ

52

ሚዛን የካቲት 8/2011 በካፋ፣ ሸካ፣ ቤንች ማጂ ዞኖችና ኮንታ ልዩ ወረዳ የማህበራዊ ጤና መድህን አፈጻጸም ዝቅተኛ መሆኑ የኢትዮጵያ ጤና መድህን ኤጀንሲ አስታወቀ።

በኤጀንሲው የሚዛን ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ሥራ አስኪያጅ አቶ ታከለ ታደሰ ለኢዜአ እንደገለጹት በሦስቱ ዞኖችና በኮንታ ልዩ ወረዳ በሚገኙ 11 ወረዳዎች የማህበራዊ ጤና መድህን አገልግሎት ያለው ሽፋን 35 በመቶ ነው።

ህብረተሰቡ ስለ ማህበራዊ ጤና መድህን አገልግሎት ያለው ግንዛቤ ዝቅተኛ መሆንና የመድኃኒት አቅርቦት እጥረት ለአፈጻጸሙ ማነስ ምክንያት መሆኑንም ጠቁመዋል።

"የግንዛቤ ችግሩ እንዲቀረፍና ህብረተሰቡ በአነስተኛ ወጪ የጤና አገልግሎት ተጠቃሚ እንዲሆን ከየዞኖቹ አመራሮችና የአስተዳደር አካላት ጋር በቅንጅት እየተሰራ ነው ብለዋል። 

አገልግሎቱን የሚሰጡ የጤና ተቋማትም በቂ የመድኃኒት አቅርቦት እንዲኖራቸው ትኩረት መስጠቱን ነው ሥራ እስኪያጁ የገለጹት።

አገልግሎት በጀመሩ 11 ወረዳዎች የጤና መድን አባላት ቁጥር  ከ72 ሺህ በላይ ማድረስ መቻሉን ጠቁመው ከአባላቱ መዋጮና መመዝገቢያ የተሰበሰበው ብር ከ10 ሚሊዮን ብር በላይ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ከተሰበሰበው የአባላት መዋጮ ውስጥም ከ5 ሚሊዮን ብር በላይ ለአባላት ህክምና መዋሉን ገልጸዋል።

በሁሉም ዞኖች በሚገኙ 26ት ወረዳዎች ላይ የማህበራዊ ጤና መድህን አገልግሎት ለማስጀመር እየተሰራ መሆኑን አመልክተዋል።

በደቡብ ቤንች ወረዳ የደብረወርቅ ቀበሌ ነዋሪ አቶ ማቲዎስ ኮምቴስ የማህበራዊ ጤና መድህን አባል በመሆናቸው መጠቀማቸውን ተናግረዋል።

"እኔን ጨምሮ የአካባቢያችን ነዋሪዎች ስለ አገልግሎቱ በቂ ግንዛቤ አልነበረንም" ያሉት አቶ ማቲዎስ፣ አገልግሎቱን በተመለከተ በባለሙያ በተደረገላቸው ገለጻ አባል መሆናቸውን ተናግረዋል።

በእዚህም ልጃቸው ሲታመም በጤና መድህኑ አገልግሎቱ ከሦስት ሺህ ብር በላይ ዋጋ ያለው የህክምና አገልግሎት ማግኘታቸውን ገልጸዋል፡፡

የቂጤ ከተማ ነዋሪ የሆኑት ወይዘሮ ወርቄ ያሽኩ በበኩላቸው በጤና መድህን ዋስትና መርሃ ግብር በመታቀፋቸው የህክምና ወጪቸው ተሸፍኖላቸው መታከማቸውን አስረድተዋል።

ቀደም ሲል በአቅም አጥረት ምክንያት በተለይ ከፍ ያለ ወጪ የሚጠይቅ ህክምና ለማግኘት ይቸገሩ እንደነበር አስታውሰው በአሁኑ ወቅት ይህ ችግራቸው በጤና መድህን አገልግሎት መፈታቱን አመልክተዋል። 

ሁሉም ነዋሪ የአገልግሎት ተጠቃሚ መሆን እንዲችል መንግስት እየሰጠ ያለውን የግንዛቤ ማስጨበጫ ትምህርት አጠናክሮ እንዲሰጥ ጠይቀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም