ኤጀንሲው ለፈተና የሚያስፈልጉ ቁሳቁሶች በሁሉም ፈተና ጣቢያዎች መድረሳቸውን ገለጸ

68
አዲስ አበባ ግንቦት 21/2010 የ10ኛ ክፍል ማጠቃለያ ፈተናና የ12ኛ ክፍል ወደ ዩኒቨርሲቲ መግቢያ ፈተና  አስፈላጊ ቁሳቁሶች በሁሉም ፈተና ጣቢያዎች መድረሳቸውን የአገር አቀፍ የትምህርት ምዘናና ፈተናዎች ኤጀንሲ  ገለፀ። የ10ኛ ክፍል ማጠቃለያ ፈተና ከነገ ጀምሮ እስከ አርብ ለሶስት ቀናት የ12ኛ ክፍል ወደ ዩኒቨርሲቲ መግቢያ ፈተና ደግሞ ከግንቦት 27 እስከ 30 ለአራት ቀናት ይሰጣል። የኤጀንሲው ዋና ዳይሬክተር አቶ አርዓያ ገብረ እግዚአብሄር የፈተና ዝግጅቱን አስመልክቶ ዛሬ በሰጡት መግለጫ 1 ሚሊዮን 222 ሺህ 757 የ10ኛ ክፍል ተማሪዎችና 284 ሺህ 558 የ12ኛ ክፍል ተማሪዎች ለፈተና እንደሚቀርቡ ተናግረዋል። ለዚህም በአገሪቱ ለ10ኛ ክፍል 2ሺህ709 የፈተና ጣቢያዎች፣ ለ12ኛ ክፍል ደግሞ 993 የፈተና ጣቢያዎች የተዘጋጁ ሲሆን ከፈተና ጋር ቀጥታ ግንኙነት ያላቸውን 55 ሺህ መምህራን ጨምሮ 77 ሺህ 22 የሰው ሀይል በየፈተና ጣቢያዎች መድረሳቸውን ገልጸዋል። የፈተና ጣቢያዎቹ በ131 ክላስተር ተመድበው የፈተና ጥያቄና የመልስ መስጫ ወረቀቶች ለፈተና የሚያስፈልጉ ቁሳቁሶች በሁሉም የፈተና ጣቢያዎች በተሟላ መልክ እንደደረሱ አረጋግጠዋል። 'ዘንድሮ በተለየና በተረጋጋ መልኩ ዝግጅት ተደርጓል፤ ፈተናዎቹ በጥንቃቄ በየጣቢያዎቹ ስለደረሱ የፈተና ደንብ ጥሰት እንዳይፈጠር ሀላፊነቱ የማህበረሰቡ፣ የፀጥታ አካላት፣ የተማሪዎችና የወላጆች መሆኑን ጠቁመው 'የፈተና ሂደቱ እንዳይስተጓጎል ሁሉም የበኩሉን ሊወጣ ይገባል' ብለዋል። በፈተና ወቅት ለሚያጋጥሙ ችግሮች ፈጣን ምላሽ የሚሰጥ ከፖሊስ፣ ከትምህርት ሚኒስቴር፣ ከመስተዳድር አካላት የተወጣጣ ግብረ ሀይል መቋቋሙን በየፈተና ጣቢያዎች ክትትል እንደሚያደርግ እና ለሚፈጠሩ ችግሮችም ፈጣን ምላሽ ለመስጠት እንደተዘጋጀ ተናግረዋል። የ8ኛ ክፍል ክልላዊ ፈተና ከሰኔ 11 እስከ 13 እንደሚሰጥ ጠቁመዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም