በማዕከላዊ ጎንደር ዞን ትምህርት ቤቶችን በመጠቀም የትራኮማ በሽታን ስርጭት ለመቆጣጠር እየተሰራ ነው

2037

ጎንደር  ግንቦት 21/2010 በማዕከላዊ ጎንደር ዞን የትራኮማ በሽታን ስርጭት ለመቆጣጠር በትምህርት ቤቶች በተቋቋሙ የትራኮማ ክበባት የግንዛቤና የቅድመ መከላከል ሥራ መጀመሩን የዞኑ ትምህርት መምሪያ አስታወቀ፡፡

በማዕከላዊ ጎንደር ዞን የሚንቀሳቀሱ 30 መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች የአጋርነት የምክክር መድረክ ትናንት በጎንደር ከተማ ተካሂዷል፡፡

በመምሪያው የስርአተ ትምህርት ዝግጅትና ትግበራ ቡድን መሪ አቶ መለሰ በሪሁን በመድረኩ እንደተናገሩት በዚህ ዓመት ወደ ሙሉ ትግባራ የገባው የዓይን ትራኮማ በሽታ መከላከል መርሃ ግብር 318ሺህ ተማሪዎችን ተደራሽ የሚያደርግ ነው፡፡

መርሀ ግብሩ የትምህርትና ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ተቋማት ከካርተር ሴንተር ጋር በመተባበር የሚያካሄዱት ሲሆን እድሜአቸው ከ10 ዓመት በታች የሆኑ የአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪዎችን ያቀፈ መሆኑን አመልክተዋል፡፡

መርሀ ግብሩ በዞኑ ከሚገኙ አንድ ሺህ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤቶች በ486ቱ መጀመሩን የገለጹት ቡድን መሪው በቀጣዩ ዓመት ደግሞ በቀሪ 514 ትምህርት ቤቶች እንደሚጀመር ገልጸዋል፡፡

እንደአቶ መለሰ ገለጻ፣ የመርሀ ግብሩ ዋና ዓላማ ተማሪዎች የዓይን ትራኮማ በሽታ መዛመቻና መከላከያ መንገዶችን በሚገባ ተገንዝበው የግል ንጽህናቸውን በመጠበቅ በበሽታው እንዳይጋለጡ ማድረግ ነው፡፡

ለመርሃ ግብሩ ተግባራዊነት በትምህርት ቤቶቹ የትራኮማ ክበባትን ከማቋቋም ጀምሮ ከካርተር ሴንተር ጋር በመተባበር ከ2 ሺህ በላይ የሳይንስ ትምህርት መምህራን ስልጠና እንዲያገኙ ተደርጎ ወደሥራ እንዲገቡ መደረጉን ገልጸዋል፡፡

የትራኮማ በሽታን ከምንጩ መከላከልና መቆጣጠር እንዲቻል በትምህርት ቤቶች የቅድመ መከላከል ሥራ ማካሄድ ተገቢ መሆኑን የገለጹት ደግሞ በካርተር ሴንተር የጎንደር አስተባባሪ አቶ ይብለጥ ዳኘው ናቸው፡፡

በዞኑ የትራኮማ በሽታን ስርጭት ለመቆጣጠር ከትምህርት ተቋማትና ከመምህራን ጋር በቅንጀት እየተሰራ መሆኑንም አስታውቀዋል።

ተማሪዎች ስለበሽታው በቂ ግንዛቤ እንዲኖራቸው በክልሉ ትምህርት ቢሮ ባለሙያዎች ተዘጋጅተው በማዕከሉ ወጪ የታተሙ የማጣቀሻ መጻህፍት ለአንድ ሺህ ትምህርት ቤቶች መሰራጨታቸውንም ተናግረዋል፡፡

“በትምህርት ቤቶቹ የግንዛቤ ትምህርት ከመስጠት ጀምሮ በትራኮማ በሽታ ተጋላጭ የሆኑ ተማሪዎች በአቅራቢያቸው በሚገኙ የጤና ተቋማት የሕክምና እርዳታ የሚያገኙበት ስርአት ተመቻችቷል” ብለዋል፡፡

አቶ ይበልጥ እንዳሉት የካርተር ሴንተር ባለፉት ሦስት ዓመታት በማዕከላዊ፣ በሰሜንና በደቡብ ጎንደር ዞኖች 2 ሚሊዮን ለሚሆኑ የትራኮማ በሽታ ተጋላጭ የሕብረተሰብ ክፍሎች በእንክብልና በቅባት መልክ የተዘጋጁ የመከላከያ መድኃኒት ሰጥቷል፡፡

“በዞኖቹ በበሽታው ምክንያት በዓይን ቆባቸው ላይ ጉዳት ለደረሰባቸው ከ5ሺህ በላይ የዓይን ሕሙማን የዓይን ቆብ ቀዶ ሕክምና ያገኙ ሲሆን ሌሎች የዓይን ቀዶ ሕክምና የሚያስፈልጋቸው ከ37ሺህ በላይ ሕሙማንም ይገኛሉ” ብለዋል፡፡

የማዕከላዊ ጎንደር ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ብርሃኑ ጣምያለው በበኩላቸው የምክክር መድረኩ መንግስትና መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ተቀራርበው በመስራት የህዝቡን የልማት ጥያቄዎች በጋራ ሆነው ደረጃ በደረጃ እንደፊቱ ማስቻሉን ተናግረዋል፡፡

የካርተር ሴንተር የአይን ትራኮማ በሽታን ስርጭት ለመቆጣጠር በትምህርት ቤቶች ደረጃ የጀመረው መርሃ ግብር እንዲሳካ መስተዳድሩ ተገቢውን እገዛና ድጋፍ እንደሚያደርግም አረጋግጠዋል፡፡

በማዕከላዊ ጎንደር ዞን በትምህርት፣ በጤና፣ በንጹህ መጠጥ ውሃና በሌሎችም የልማት ዘርፎች የተሰማሩ ከ30 በላይ መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች እንደሚገኙ ለማወቅ ተችሏል ፡፡