በኢትዮጵያ የታየው ለውጥ በአፍሪካ ኢኮኖሚና ፖለቲካ ላይም ለውጥ እያመጣ ነው

138

አዲስ አበባ የካቲት 7/2011በኢትዮጵያ የታየው ለውጥ በአፍሪካ ኢኮኖሚና ፖለቲካ እጣ ፋንታም ላይ ለውጥ እያመጣ መሆኑን በኢትዮጵያ የዛምቢያና የላይቤሪያ አምባሳደሮች ተናገሩ።

በኢትዮጵያ የፖለቲካ ለውጥ ከመጣ በኋላ በአፍሪካ በተለይም በምስራቅ አፍሪካ ቀጣና በሚገኙ አገራት መካከል የኢኮኖሚ ፣ የፖለቲካና የማህበራዊ ትስስር እንዲኖር ምቹ ሁኔታ ተፈጥሯል ብለዋል።

አገሪቷ በቀጣናው ሰላምና መረጋጋት በማምጣት ረገድ ያላት ተሳትፎ ትልቅ እንደነበረና በአሁኑ ወቅትም ከአጎራባች አገራት ጋር ሰላም በማምጣት እንዲሁም አንድነትን በማጠናከር ረገድ የጎላ ሚና እየተጫወተች መሆኗን ተናግረዋል።

አምባሳደሮቹ አገሮቻቸውን ወክለው በኢትዮጵያ ሲያገለግሉ የቆዩ ሲሆኑ የስራ ጊዜያቸውን አጠናቀው ዛሬ ከፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ የስንብት ደብዳቤያቸውን ተቀብለዋል።

በኢትዮጵያ የዛምቢያ አምባሳደር የነበሩት ሱዛን ሲክኔታ ከስንብቱ በኋላ እንዳሉት የፖለቲካ ለውጡ ለኢትዮጵያዊያን ብቻም ሳይሆን ለአፍሪካዊያን ለውጥ እያመጣ ያለና 'ልንደግፈው የሚገባ ነው' ብለዋል።

በቀጣይም 'በሄድንበትና ባለንበት ቦታ ሁሉ ለውጡ እንዲቀጥል ከኢትዮጵያዊያንና ከኢትዮጵያ መንግስት ጎን ሆነን እንሰራለን' ሲሉም ተናግረዋል።

የስንብት ደብዳቤያቸውን የተቀበሉት በኢትዮጵያ የላይቤሪያ አምባሳደር ጆርጅ ፔተን በበኩላቸው ኢትዮጵያ በአፍሪካ ያላት ሚና እያደገ መሆኑን ገልጸዋል።

በቀጣይ በሚሰሩበት ቦታም በኢትዮጵያና በላይቤሪያ የሁለትዮሽ ትስስር ብቻም ሳይሆን በአህጉራዊ ጉዳዮች ጭምር 'አብረን እንሰራለን' ነው ያሉት።

ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ በበኩላቸው ኢትዮጵያ የአፍሪካ አገራት ትስስር ወደ ላቀ ደረጃ እንዲደርስ በአፍሪካ ህብረት ማዕቀፍ ስር ትልቅ ትኩረት ሰጥታ እንደምትሰራ መግለጻቸውን የስንብት ስነ-ስርዓቱን የተከታተሉት የፕሬዚዳንት ጽህፈት ቤት የፕሮቶኮልና ኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ አሸብር ጌትነት ተናግረዋል።

የአገራቱ ተተኪ አምባሳደሮችም ከሁለትዮሽ ግንኙነቱ ጎን ለጎን የአፍሪካዊያን የኢኮኖሚ፣ የፖለቲካና የማህበራዊ ትስስር እንዲጠናከር የበኩላቸውን እንደሚወጡ እምነታቸው መሆኑን ፕሬዚዳንቷ ገልጸውላቸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም