በአንዳንድ ቦታዎች በመስጂድ አካባቢ እየታየ ያለው አለመግባባት እንዲቆም ጥሪ ቀረበ

74

አዲስ አበባ ጥር 7/2011በአንዳንድ ቦታዎች በመስጂድ አካባቢ እየታየ ያለው አለመግባባት እንዲቆም የኢትዮጵያ ሙስሊሞች ተቋማዊ ለውጥ የጋራ ኮሚቴ ጥሪ አቀረበ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድና ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን  የኢትዮጵያ ሙስሊሞች ተቋማዊ ለውጥ የጋራ ኮሚቴ አባላት ጋር ትናንት ተወያይተዋል።

ኮሚቴው ውይይቱን አስመልክቶ በቀዳሚ ሙፍቲ ሃጂ ዑመር እንድሪስ አማካኝነት ዛሬ መግለጫ ሰጥቷል።

በመግለጫው ላይ እንደተጠቀሰው ኮሚቴው ከተመረጠበት ሰኔ ጀምሮ እስካሁን ያከናወናቸውን ተግባራት ለጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ፣ ለምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንንና ለሰላም ሚኒስትሯ ወይዘሮ ሙፈሪያት ካሚል ገለጻ አድርጓል።

የህግ ጉዳይ ፣ የመጅሊስ አወቃቀር እንዲሁም ሸሪአ ወይም የሃይማኖት መመሪያን የተመለከቱ ጉዳዮች ላይ ከሚመለከታቸውን አካላት ጋር በመሆን ስራዎች ሲከናወኑ መቆየታቸውን ነው የገለጹት።

በአንዳንድ ቦታዎች በመስጂድ አካባቢ እየታየ ያለው አለመግባባት እንዲቆምም ነው ቀዳሚ ሙፍቲ ሃጂ ዑመር እንድሪስ ጥሪ ያቀረቡት።

ኢትዮጵያ ለዘመናት የቆየውን የመከባበርና መተጋገዝ እሴት በማስጠበቅ ህዝበ ሙስሊሙ ከአላስፈላጊ ተግባራት እንዲቆጠብም ጠይቀዋል።

ቀዳሚ ሙፍቲ ሃጂ ዑመር እንደገለጹት መጥፎ ተግባር መፈጸም በየትኛውም ሃይማኖት የተወገዘ ነው ፤ አንዱ የአንዱን እምነት ማክበርና በሰላም መኖርም ይገባዋል።

ትናንት በጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት በተካሄደው ውይይት ላይ ዶክተር አብይ ኮሚቴው ያስመዘገባቸውን ውጤቶች እንዲያጠናክር አቅጣጫ የሰጡ ሲሆን ፤ እርሳቸውም የበኩላቸውን ድጋፍ እንደሚያደርጉ መግለጻቸው ተዘግቧል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከሁለት ወር በፊት ከኮሚቴው ጋር ባካሄዱት ውይይት መግባባቶችን ለማጠናከር እንዲሁም የኮሚቴውን ጥረት ለማደናቀፍ የሚሰሩ ማናቸውንም እንቅፋቶች በመከላከል የመንግስት ድጋፍ እንደማይለያቸው መግለፃቸውም ይታወሳል።

የኢትዮጵያ ሙስሊሞች ተቋማዊ ለውጥ የጋራ ኮሚቴ በቅርቡ ከ300 በላይ ከሚሆኑ ዑላማዎችን ፣ ምሁራንና ከሚመለከታቸውን አካላት ጋር የመጅሊሱ ምርጫን ጨምሮ በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ውይይት ያካሂዳል ተብሎ ይጠበቃል።

የኢትዮጵያ ሙስሊሞች ተቋማዊ ለውጥ የጋራ ኮሚቴ ያዋቀራቸዉ አራት ንዑሳን ኮሚቴዎች እንዳሉት ይታወቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም