የአውሮፓ ህብረት በዚምባብዌ አጠቃላይ ምርጫ ታዛቢዎቹን ይልካል - ኢዜአ አማርኛ
የአውሮፓ ህብረት በዚምባብዌ አጠቃላይ ምርጫ ታዛቢዎቹን ይልካል

ግንቦት 21/2010 ዚምባብዌ በመጪው ሃምሌ ወር በምታካሂደው አጠቃላይ ምርጫ የአውሮፓ ህብረት ታዛቢዎችን ለምልከታ እንዲያሰማራ የመግባቢያ ስምምነት ተፈራርማለች። የመግባቢያ ስምምነቱን የተፈራረሙት የዚምባብዌ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሲቡሲሶ ሞዮ እና በዚምባብዌ የአውሮፓ ህብረት ልዑክ መሪ ፊሊፔ ቫን ዳሜ ናቸው። በዚህም መሰረት ህብረቱ ከ16 ዓመት ወዲህ በዚምባብዌ ምርጫ ታዛቢዎቹን ለመጀመሪያ ጊዜ ያሰማራል ነው የተባለው። የመግባቢያ ስምምነት ሰነዱ ለምርጫ ሂደቱ ታዛቢዎች መመሪያዎችን ያካተተ ነው። የዚምባብዌ መንግስት በሀገሪቱ በሚካሄደው ምርጫ ላይ የአውሮፓ ህብረት ታዛቢዎቹን እንዲለክ ባለፈው መጋቢት ወር በይፋ መጋበዙ ይታወቃል። ለረጅም ዓመታት ዚምባብዌን ሲመሯት የቆዩት ሮበርት ጋብሬል ሙጋቤ ባለፈው ህዳር በወታደራዊ ሃይሉ ከስልጣን ከወረዱ በኋላ በሀገሪቱ ምርጫ ሲካሄድ የመጀመሪያው ይሆናል። ሙጋቤን ተክተው የዚምባብዌ ፕሬዝዳንት የሆኑት ኤመርሰን ምናንጋግዋ ከ“ሙቭመንት ፎር ዴሞክራቲክ ቼንጅ” የተቃዋሚ ፓርቲ እጩ ኔልሰን ቻሚሳ ጋር በምርጫው ይፎካከራሉ። ምናንጋግዋ በሀገሪቱ ነፃና ፍትሃዊ ምርጫ እንደሚካሄድ ቃል ገብተዋል። በዚምባብዌ የአውሮፓ ህብረት ልዑክ መሪ ፊሊፔ ቫን ዳሜ ህብረቱ የሀገሪቱ መንግስት ለሰላማዊ፣ ተዓማኒ፣ አሳታፊ እና ግልፅ ምርጫ ያለውን ቁርጠኝነት እንደሚያደንቅ መናገራቸውንም የቻይናው ዓለም ዓቀፍ ቴሌቪዥን ኔትዎርክ አስነብቧል።