ሉክሰምበርግ ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን የኢኮኖሚ ትብብር ይበልጥ ለማጠናከር ትሻለች

71

አዲስ አበባ የካቲት 6/2011 ሉክሰምበርግ ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን የኢኮኖሚ ትብብር ይበልጥ ማጠናከር እንደምትሻ የአገሪቷ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ገለፁ።

የኢፌዲሪ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ወርቅነህ ገበየሁ ከሉክሰምበርግ አቻቸውና የአውሮፓ ጉዳዮች ሚኒስትር ዣን አሰልቦርን ጋር በፅህፈት ቤታቸው ተወያይተዋል።

ሚኒስትሮቹ በውይይታቸው በዋነኝነት የሁለቱን አገሮች ግንኙነትና የኢኮኖሚ ትስስር ይበልጥ ማጠናከር በሚቻልበት ሁኔታ ላይ መምከራቸውን የኢፌዲሪ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ፅህፈት ቤት በመረጃው ጠቅሷል።

ሁለቱ አገሮች በተለይ ኢኮኖሚያዊ ትስስሩን ይበልጥ ለማጎልበት የተደራራቢ ቀረጥ ማስወገጃ ስምምነት፣ የአየር ትራንስፖርት ስምምነት ማደርግ በሚቻልበት ጉዳይም መክረዋል።

ሉክሰምበርግ በፋይናንስና ባንኪንግ ዘርፍ ያላትን ሰፊ ልምድና ተሞክሮ ለኢትዮጵያዊያን ባለሙያዎች ማካፈል በምትችልበት ሁኔታ ላይም መምከራቸው ታውቋል።

የሉክሰምበርግ የውጭ ጉዳይና የአውሮፓ ጉዳዮች ሚኒስትር የሆኑት ዣን በኢትዮጵያ የሚገኙ የስደተኛ ካምፖችን ተዘዋውረው የጎበኙ ሲሆን ኢትዮጵያ ስደተኞችን በማስተናገድ ረገድ በቅርቡ ያሳለፈችውን የህግ ማሻሻያም አድንቀዋል።

ኢትዮጵያና ሉክሰምበርግ ጠንካራ ዲፕሎማሲያዊ ግንኑነት ያላቸው ሲሆን ሉክሰምበርግ ኤምባሲዋን በ2004 ዓ.ም በአዲስ አበባ ከፍታለች።

በብራስልስ የሚገኘው የኢፌዲሪ ኤምባሲም ሉክሰምበርግን ጨምሮ የዲፕሎማሲ ስራውን በማከናወን ላይ ይገኛል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም