ዕርቅ በማውረድ ያገኘነውን ሠላም አጠናክረን ለማስቀጠል በጋራ እንሰራለን....የጌዴኦና የጉጂ ኦሮሞ አባ ገዳዎች

133
ዲላ ሚያዝያ 26/2010 ዕርቅ በማውረድ ያገኘነውን ሠላም አጠናክረን ለማስቀጠል በጋራ እንሰራለን ሲሉ የጌዴኦ እና የጉጂ  ኦሮሞ አባ ገዳዎች ተናገሩ ፡፡ አባ ገዳዎቹ ይህን ያሉት በጌዴኦና በምዕራብ ጉጂ ዞኖች አዋሳኝ አካባቢ በቅርቡ ተፈጥሮ የነበረውን የፀጥታ ችግር ለመፍታት ባህላዊ የዕርቅ ሥርአት በተከናወነበት ወቅት ነው ፡፡ በሁለቱም ሕዝቦች ዘንድ " ጎንዶሮ " በመባል የሚታወቀው ባህላዊ የዕርቅ ሥርአት ኤዴራ በተባለ አዋሳኝ ሥፍራ ሲከናወን የጌዴኦና የጉጂ ኦሮሞ አባ ገዳዎች፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣ ነዋሪዎች እንዲሁም የአመራር እና የፀጥታ አካላት ተገኝተዋል ፡፡ የጉጂ ኦሮሞ አባገዳ ጂሎ ማኖ በዚህ ወቅት እንዳሉት የጌዴኦ አባት ተብሎ የሚታወቀው « ደረሶ » እና የጉጂ ኦሮሞ አባት በመባል የሚታወቀው « ጉጆ » የአንድ እናትና አባት ልጆች እንደነበሩ ተናግረዋል ፡፡ "አንድ ቤተሰብ ነን፤ እርስ በርስ የሚያጋጨን ምክንያት የለንም " ያሉት አባ ገዳ ጂሎ ማኖ የ"ጎንዶሮ" ዕርቅ ሥርአት በመፈፀሙ ከዚህ በኋል ህዝቡ መቃቃሩን እንዲተውና እንደድሮው በወንድማማችነት ተፋቅሮ መኖር እንዳለበት አሳስበዋል ፡፡ አባ ገዳ ጂሎ ማኖ «አሁን ዕርቅ በማውረዳችን ያገኘነውን ሠላም ለማስቀጠልና የሁለቱንም ህዝቦች አንድነት ለማረጋገጥ ከጌዴኦ አባ ገዳ ጋር በጋራ እንሰራለን » ብለዋል ፡፡ በቀጣይ በደል የሚደርስበት ወገን ካለም ወደ ፀብ ከመሄድ ይልቅ ለአባገዳዎች በማሳወቅ ችግሩን በሰላማዊ መንገድ መፍታት እንዳለበት አስገንዝበዋል፡፡ የጌዴኦ አባ ገዳ ደንቦቢ ማሮ በበኩላቸው « አሁን ዕርቅ አድርገናል። ከንግዲህ ማንም ሰው ይህ ጌዴኦ ነው ፤ ይህ ጉጂ ነው ብሎ መናገርና መከፋፈል የለበትም » ብለዋል ፡፡ « ከዚህ በኋላ እጃችንን ለፀብ ሳይሆን ለልማትና ሰላም ብቻ ማንሳት ይገባናል » ያሉት አባ ገዳ ደንቦቢ ማሮ፣ ህዝቡ እንደ ቀድሞው ደስታውንና ሀዘኑን በጋራ ማሳለፍና ወንድማማችነቱን ማስቀጠል እንዳለበት መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡ አክለውም « የመለያየት ሀሳብ ዳግም በመካከላችን እንዳይፈጠር እጅ ለእጅ ተያይዘን እንሰራለን » ሲሉ አባ ገዳ ደንቦቢ ማሮ ገልጸዋል፡፡ የጌዴኦ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ኃይለማርያም ተስፋዬ በበኩላቸው የጌዴኦና የጉጂ ኦሮሞ ሕዝቦች ተመሳሳይ ባህላዊ የአስተዳደር ሥርዐትና የአኗኗር ዘይቤ ያላቸው መሆናቸው ወንድማማችነታቸውን የሚያሳይ እንደሆነ አስረድተዋል ፡፡ « ምንጊዜም ህዝብ ከህዝብ ጋር አይጋጭም » ያሉት አቶ ኃይለማርያም ሁለቱም ወገኖች የቀድሞ አብሮነታቸውን ለማስቀጠል ዕርቀ-ሠላም ማውረዳቸው በመካከላቸው ለግጭት የሚዳርግ ምክንያት እንደሌለ የሚያመላክት መሆኑን ተናግረዋል፡፡ በቀጣይ በሕዝቦች መካከል ያለውን አንድነት ይበልጥ በማጠናከር የጋራ ልማትን አጠናክሮ ለማስቀጠል ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በቅንጅት እንደሚሰራም አረጋግጠዋል ፡፡ « ዛሬ የተከናወነው የዕርቅ ሥርአት ጥገኛ ፀረ-ሠላም ኃይሎች ሁለቱን ህዝቦች መለያየት እንደማይችሉ ያሳየንበት ነው » ያሉት ደግሞ የምዕራብ ጉጂ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ አበራ ቡኖ ናቸው ፡፡ እነዚህ ኃይሎች ዳግም ህዝቡን ለተመሳሳይ ችግር እንዳይዳርጉት ማድረግ የሁሉም ኃላፊነት እንደሆነ ገልጸው፣ ዘላቂ ሠላምን ለማረጋገጥ ከህዝቡ ጋር በጋራ እንደሚሰራ አረጋግጠዋል፡፡ የኦሮሚያ ክልል አስተዳደርና ፀጥታ ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ሁሴን ፈይሶ በበኩላቸው በአካባቢው ሰላም መውረዱን ተከትሎ ህዝቡ ትኩረቱን ወደ ልማትና ዴሞክራሲ ግንባታ ሊያዞር እንደሚገባ አስገንዝበዋል ፡፡ ፀረ-ሠላም ኃይሎች ዳግም የህዝቡን ሰላም እንዳይነጥቁ ከአጎራባች ዞኖችና ክልል መንግስታት ጋር በቅንጅት እየተሰራ መሆኑንም አመልክተዋል። ለግጭት በር የሚከፍቱ የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ለመቅረፍ ከምንጊዜውም በላይ የክልሉ መንግስት ርብርብ ያደርጋል ብለዋል ፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም