ግንባታ ባልጀመሩና መሰረት ብቻ አውጥተው ወደ ግንባታ ያልገቡ የሪል ስቴቶች ይዞታቸው እንዲነጠቅ ተወሰነ

925

አዲስ አበባ የካቲት 6/2011 የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር መሬት ወስደው ግንባታ ባልጀመሩና መሰረት ብቻ አውጥተው ወደ ግንባታ ያልገቡ የመኖሪያ ቤት ገንቢ (ሪል ስቴት) ድርጅቶች ይዞታቸው እንዲነጠቅ መወሰኑን አስታወቀ።

ከተማ አስተዳደሩ በከተማዋ ውስጥ በሪል ስቴት ዘርፍ የተሰማሩ ድርጅቶችን የግንባታ ሁኔታና ህጋዊነት የሚያጠና ግብረ ሃይል አዋቅሮ የዳሰሳ ጥናት ሲያከናውን መቆየቱ ይታወሳል።

በዚህም ግብረሃይሉ በፋይልና የግንባታ ሳይት ላይ ምልከታ በማድረግ እና መጠይቆችን በመጠቀም የሪል ስቴቶቹን የህግ አግባብነት፣ የሊዝ ውል እና የግንባታ ደረጃ ሲያጣራ ቆይቶ የደረሰበትን የኦዲት ሪፖርት ዛሬ ለከተማ አስተዳደሩ አቅርቧል።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደርም ህጋዊ አግባብነት በሌላቸው እና ግንባታ ባልጀመሩ የሪል ስቴት ድርጅቶች ላይ እርምጃ እንዲወሰድ መወሰኑን ከአዲስ አበባ ከንቲባ ጽህፈት ቤት የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

በዚህም መሰረት መሬት ወስደው ግንባታ ባልጀመሩ እና መሰረት ብቻ አውጥተው ወደ ግንባታ ያልገቡ የሪል ስቴት ድርጅቶች ይዞታ ነጥቆ ወደ መሬት ልማት ባንክ ገቢ እንዲደረግና ተመላሽ የተደረገውም መሬት የቤቶች ልማት ፕሮጀክት ላይ እንዲውል ከተማ አስተዳደሩ ወስኗል።

የሪል ስቴት ድርጅቶቹ የሚገኙባቸው ክፍለ ከተሞች እስከ የካቲት 10 ቀን 2011 ዓ.ም መሬት ወስደው ግንባታ ባልጀመሩ እና መሰረት ብቻ አውጥተው ወደ ግንባታ ያልገቡ የሪል ስቴት ድርጅቶች ቁጥር አጣርተው ለከተማ አስተዳደሩ እንዲያቀርቡም መወሰኑ ተገልጿል።

በአዲስ አበባ ከተማ በሪል ስቴት የተሰማሩ 138 ድርጅቶች ይገኛሉ።