በአካባቢው በለሙ የተፋሰስ ልማት ሥራዎች ተጠቃሚ ሆነናል---በአማራ ክልል የሰሜን ሸዋ ዞን አርሶ አደሮች

75

ደብረ ብርሃን  ካቲት 6/2011 በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን የሚገኙ አርሶ አደሮች ባለፉት አምስት ዓመታት በአፈርና ውሃ ጥበቃ ሥራ በለሙ ተፋሰሶች ተጠቃሚ መሆናቸውን ገለጹ።

በዞኑ የአሳግርት ወረዳ ዳጎላ ቀበሌ ነዋሪ የሆነው አርሶ አደር ኃይሉ ግዛው ለኢትዮዽያ ዜና አገልግሎት እንደገለጹት በአካባቢው በአፈርና ውሃ ጥበቃ ሥራ በለሙ ተፋሰሶች ተጠቃሚ ሆነዋል።

ከእዚህ ቀደም የእርሻ መሬታቸው በዝናብና በንፋስ ተጠርጎ ለምነቱን በማጣቱ ከአንድ ሄክታር መሬታቸው ስምንት ኩንታል ብቻ ምርት ያገኙ  እንደነበር አስታውሰዋል።

በአፈርና ውሃ ጥበቃ ሥራ በለማው መሬታቸው ላይ የአፈር ማዳበሪያና ምርጥ ዘር ተጠቅመው ከዘሩት ሰብል በሄክታር እስከ 20 ኩንታል ምርት ማግኘታቸውን ገልጸዋል።

በተጨማሪም በአካባቢው የተቀናጀ የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ ሥራ ከተጀመረበት ጊዜ ጀምሮ በየጊዜው የመሬታቸው ለምነት እየጨመረ በመምጣቱ ከሰብል ልማቱ ጎን ለጎን በእንስሳት እርባታና በንብ ማነብ ሥራ ላይ ተሰማርተው ተጠቃሚ እየሆኑ መምጣታቸውን አስረድተዋል።

ዘንድሮ ከ8 ዘመናዊ የንብ ቀፎ ላይ ለመጀመሪያ ጊዜ 100 ኪሎ ግራም ማር በማምረት ከ20 ሺህ ብር በላይ ገቢ ማግኘታቸውን በማሳያነት ጠቅሰዋል።

ካደለቧቸው የሥጋ በሬዎችም ከ60 ሺህ ብር በላይ ገቢ ማግኘታቸውንም ነው የጠቆሙት።

በሰሜን ሸዋ ዞን በአጾኪያ ገምዛ ወረዳ የኩሬ ጎደን ቀበሌ ነዋሪው አርሶ አደር አሰፋ በቀለ በበኩላቸው ከአሁን ቀደም ከግማሽ ሄክታር መሬት ከአምስት ኩንታል ምርት በላይ እንደማያገኙ አስታውሰው አካባቢው በመልማቱ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ከእዚሁ መሬት 16 ኩንታል ምርት እያገኙ መሆናቸውን አስረድተዋል።

"በአካባቢው የደረቁ ምንጮች መልሰው አገልግሎት መስጠት መጀመራቸውን የተናገሩት አርሶ አደር አሰፋ በመስኖና በመኸር እርሻ በዓመት ከሦስት ጊዜ በላይ በማምረት የተሻለ ተጠቃሚ ሆኛለሁ" ብለዋል።

በማንጎ፣ ፓፓያ፣ ብርቱካንና ሙዝ በማልማት በዓመት እስከ 30 ሺህ ብር ተጨማሪ ገቢ  እያገኙ መሆኑን የገለጹት አርሶ አደሩ በዚህም የእርሳቸውም ሆነ የቤተሰባቸው ኑሮ መሻሻሉን ተናግረዋል። 

በሰሜን ሸዋ ዞን ግብርና መምሪያ የተፈጥሮ ሀብት ልማት ጥበቃ እና አጠቃቀም ቡድን መሪ አቶ ጌታነህ ተክለማሪያም ከአምስት አመት በፊት ከለሙት 940 ተፋሰሶች መካከል 520 ተፋሰሶች ህብረተሰቡን ተጠቃሚ ማድረግ መጀመራቸውን አስረድተዋል።

በዞኑ በለሙ ተፋሰሶች በዘላቂነት ለመጠቀም በተፋሰሶቹ የተደራጁ ማህበራት እንዲያስተዳድሯቸው ለማድረግ እንቅስቃሴ መጀመሩን ጠቁመዋል።

አቶ ጌታነህ እንዳሉት በተያዘው ዓመት ከ1 ሺህ  በላይ  በሚሆኑ ተፋሰሶች ላይ የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ ሥራ ለማከናወን ታቅዶ ወደ ሥራ ተገብቷል።

ለእዚህም ከ59 ሺህ በላይ ሄክታር መሬት በስነ ህይወታዊ ዘዴ ለማልማት 570 ሚሊዮን የዋንዛ፣ ባህር ዛፍ፣ ግራር፣ ወይራና ኮሶ እንዲሁም ለእንስሳት መኖ የሚውሉና ለአፈርና ውሃ ጥበቃ ሥራው አጋዥ የሆኑ ችግኞችን የማዘጋጀት ሥራ እየተከናወነ መሆኑን አስረድተዋል።

በወልና በግል ይዞታ መሬት የተተከሉ ችግኞችን በመንከባከብ እና አዳዲስ  መሬቶችን በማልማት የደን ሽፋኑን በቀዳሚው ዓመት ከነበረበት  15 ከመቶ ወደ 16 ነጥብ 2 ከመቶ ለማድረስ  እየተሰራ መሆኑንም አቶ ጌታነህ  ጠቁመዋል።

በዞኑ ተራራማ አካባቢዎች በለሙ ተፋሰሶች 400 የሚደርሱ የአካባቢው ወጣቶችን በአትክልትና ፍራፍሬ ልማት በመደራጀት ወደ ሥራ መግባታቸውን ከዞኑ ግብርና መምሪያ የተገኘ መረጃ ያመለክታል ሲል የዘገበው አዜአ ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም